የቁሳቁስ እጥረት የደም ማሰባሰብ ተግባሩ ላይ ጫና እየፈጠረብኝ ነው - ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት

60

አዲስ አበባ መጋቢት 11/2011የበጎ ፈቃደኞች ደም የመለገስ ባህል እየዳበረ ቢመጣም ደም ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በበቂ መጠን ማግኘት ባለመቻሉ ደም የማሰባሰብ ተግባሩ ላይ ጫና እየተፈጠረበት እንደሆነ ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ገለጸ።

የደም ባንክ አገልግሎቱ የክልል ቅርንጫፎች በከፍተኛ ደረጃ የደም ማሰባሰቢያ ቁሳቁስ እጥረት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

በክልሎች በሚገኙ 25 የደም ባንኩ ቅርንጫፎች ደም የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ ለጤና ተቋማት እያዳረሰ ቢሆንም በበቂ መጠን እያሰራጨ እንዳልሆነ አመልክቷል።

ይህ የሆነበት ምክንያት ደም የመለገስ ፍላጎት ካላቸው ዜጎች ጋር የሚመጣጠን ደም ለመሰብሰብ የሚያስችል ቁሳቁስ ቅርንጫፎቹ ለማግኘት እየተቸገሩ እንደሚገኙ ገልጿል።

በብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች ቡድን መሪ አቶ ዘላለም ካሳዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዜጎች በበጎ ፈቃደኝነት ደም የመለገስና የማስተባበር ባህል አድጓል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ ወጣቶች ከሚያከናውኑት ተግባራት መካከል የደም ልገሳ ማከናወንና የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማዳበር ትልቁን ድርሻ የሚወስድ በመሆኑ የለጋሹ ቁጥር ማደጉን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የደም መመርመሪያ ኪቶች፣ ደም የመሰብሰቢያ ከረጢቶችና የተለያዩ ግብአቶች በበቂ ሁኔታ ባለመሟላታቸው በሚፈለገው መጠን ከለጋሾች ደም ለመሰብሰብ አዳጋች እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ቁሳቁሶቹ በአገር ውስጥ የማይመረቱ በመሆናቸው ከውጭ ግዢ ለመፈፀም በሚያጋጥሙ ውስብስብ አሰራሮች የተነሳ ቁሳቁሶቹ በወቅቱ እንዳይገዙና ተደራሽ እንዳይሆኑ እንቅፋት ስለመሆኑ ገልጸዋል።

እጥረቱን ለመፍታት በደም ባንኩ፣ በክልል ጤና ቢሮዎችና በመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ጋር እየሰራ ቢሆንም ችግሩን መፍታት አልተቻለም።

ቅርንጫፎቹ ከመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ (ፒኤፍኤስኤ) የደም መሰብሰቢያ ቁሳቁስ እንዲወስዱ እየተደረገ ቢሆንም በበቂ መጠን አለመቅረቡ ሊፈታ እንዳልቻለ አቶ ዘላለም ጠቁመዋል።

''ችግሩ በክረምትና በበጋ ወቅት ከደም ባንኩ ጋር በመቀናጀት ደም የመለገስና የማሰባሰብ ተግባርን እያከናወኑ ላሉ በጎ ፍቃደኞች ተሳትፏቸውን እንዳያጎለብቱ እንቅፋት እየሆነ ነው ያሉት'' ቡድን መሪው እጥረቱ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዘንድ ቅሬታን እየፈጠረ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት እየጨመረ የመጣው የደም ፍላጎት በደም ባንኮች ካሉ ሙያተኞችና ግብአት ጋር ባለመመጣጠኑ ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢዜአ መድሃኒትና ሌሎች የህክምና መሳሪያዎችና ቁሳቁሶችን ወደአገር የማስገባት ሃላፊነት የተጣለበትን የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲን የስራ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ጊዜ በስልክና በአካል ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ምላሹን ማካተት አልተቻለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም