ግብፅ በመገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር የሚፈቅድ ህግ ወደ ተግባር አስገባች

76

መጋቢት 11/2011 ሀገሪቱ ወደ ተግባር ያስገባችው አዲሱ ህገ መንግስት ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ድረገፆችንና ማህበራዊ ትስስር ገፆችን እንዲያግድ የሚያስችል ነው ተብሏል።

የግብፅ የሚዲያ ተቆጣጣሪ ተቋም ገቢራዊ ያደረገው ህግ ከ5 ሺህ በላይ ተከታይ ያላቸው ድረገጾችና ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት ከሆኑ እንዲታገዱ የሚያደርግ ነው።

ትናንት ተግባራዊ መሆን የጀመረው ህግ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ የሀሳብ ልዩነትን የመግለፅ ነጻነት ላይ ጫና ለማሳደር ከሚወስዱት እርምጃ አንዱ ነው በሚል እየተተቸ ነው።

ግብፅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመገናኛ ብዙሃንና በጋዜጠኞች ላይ ድንገተኛ  ፍተሻ የጀመረች ሲሆን በርካቶችን ለእስር የውጭ ሀገር ጋዜጠኞችን የማባረር ስራ ትሰራለች።

አዲሱ ህግ የሀገሪቱ የሚዲያ ተቆጣጣሪ  ምክር ቤት ሀሰተኛ መረጃ ያሰራጫሉ የሚላቸውን ድረገጾችና ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲያግድ የሚፈቅድ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ሀሰተኛ መረጃ በሚያሰራጩት ላይ የፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይጠበቅበት 14 ሺህ 400 የአሜሪካ ዶላር ቅጣት እንዲጥልም ለምክር ቤቱ ስልጣን ሰጥቶታል።

ታዋቂ የግብፅ ጋዜጠኞች የመንግስት ውሳኔ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ብለዋል።

በምክንያትነት ያቀረቡትም ህጉ ለተቆጣጣሪ ምክር ቤቱ ሚዲያዎችን ሳንሱር የማድረግ ከፍተኛ ስልጣን ሰጥቶታል፤ ይህ ደግሞ የፕረስ ነጻነትን ይጋፋል የሚል ነው።

የተቆጣጣሪ ምክር ቤቱ ሊቀመንበር ማክራም ሞሃመድ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ባለዘጠኝ ገፁ አዋጅ በውስጡ በርካታ ክልከላዎችን የጣለ ሲሆን የህግ ጥሰትን፣ የህዝብ ሞራል ዝቅ ማድረግን ዝረኝነትን፣ ግጭት፣ በዜጎች መካከል መገለልና ጥላቻን መስበክን ይከለክላል።

በህጉ መሰረት ጥቃትና ትንኮሳ የሚቀሰቅሱ መረጃዎችን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙሃን 5 ሚሊየን የግብፅ ፓውንድ ወይም 298 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ጋዜጦችን እና ድረገጾችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማገድ በህገመንግሥቱ የተከለከለ ነው ያሉት የጋዜጠኞች ህብረት አባል ገማል አብደል ራሂም ናቸው።

ገማል እንደሚሉት በህገመንግሥቱ መሠረት አሁን ለሚዲያ ተቆጣጣሪ ምክር ቤቱ የተሰጠው ስልጣን ህጋዊ አይደለም።

የሚዲያ ተቆጣጣሪ  ምክር ቤቱ በአዲሱ ህግ ተግባራዊነት ላይ የጋዜጠኞች ህብረት ያቀረባቸውን አስተያየቶች ውድቅ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ግብፅ ውስጥ ከ2017 መጨረሻ ጀምሮ 500 ያህል ድረገጾችና የዜና ማሰራጫዎች መታገዳቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የግብፅ ባለስልጣናት በበኩላቸው ሀገሪቱ ወደ አለመረጋጋት እንዳትገባ፣ በሰሜናዊ ሲናይ አመፅን ለማስወገድና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ህጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ምንጭ፦አልጀዚራ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም