በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለ የሊፍት መወጣጫ ተደርምሶ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ

46

አዲስ አበባ  መጋቢት 11/2011 በአዲስ አበባ አዲስ እየተገነባ ለሚገኝ ህንጻ እየተገጠመ ያለ የአሳንሰር (ሊፍት) መወጣጫ ተደርምሶ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ።

በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ላፍቶ ሞል አካባቢ ትናንት በደረሰው አደጋ ሌሎች አራት ሰዎች መጎዳታቸውም  ታውቋል ።

አደጋው የደረሰው ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ባለው ባለ16 ወለል ህንጻ ሊፍት (አሳንሰር) ለመስራት ተብሎ የተገጠመው  መወጣጫ በመውደቁ  መሆኑን የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጄንሲ አስታውቋል።

አደጋው ትናት ጠዋት 3 ሰዓት የተከሰተ ሲሆን ሁለተኛውን አስክሬን ለማውጣት   እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት የህይወት አድን ስራው መከናወኑን የኤጀንሲው ኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልፀዋል።

አሳንሰሩ የሚገነባበት ቦታ ጠባብ በመሆኑ የተነሳ የህይወት አድን ሥራውን ከባድ እንዳደረገውና ረጅም ጊዜ እንደፈጀ ተናግረዋል።

በአደጋው የሞቱትና ጉዳት የደረሰባቸው በህንፃው ግንባታ የተሰማሩ የቀን ሠራተኞች ናቸው።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአለርት ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑም ታውቋል።

አደጋው የደረሰባቸው ሰራተኞች በወቅቱ ምንም አይነት የአደጋ መከላከያ መሳሪያ አላደረጉም ነበር ያሉት ባለሙያው በግንባታ ሥራ የሚሰማሩ ሰራተኞች  መከላከያ ቢጠቀሙ የሚደርሱ አደጋዎችን መጠን መቀነሰ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም