ኤርትራ የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ ሆነች

61

ባህር ዳር መጋቢት 10/2011 በባህር ዳር ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው 14ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና ውድድር በኤርትራ አጠቃላይ አሸናፊነት ዛሬ ተጠናቀቀ።

ከመጋቢት 5/ 2011ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው በዚሁ ውድድር 13 የአፍሪካ ሀገራት ተሳትፈዋል፡፡

በዚህም  የኤርትራ ብስክሌት ቡድን በሰባት የወርቅ፣በስድስት  የብር እና በአራት ነሐስ ሜዲሊያዎች አንደኛ  ሆኖ አጠናቋል፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ ሰባት የወርቅ፣ አምስት የብር እና ሁለት የነሐስ  ሜዲሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃላች፡፡

የሩዋንዳ ብስክሌት ቡድን በበኩሉ ሁለት የወርቅ እና ሶስት የነሐስ   ሜዲሊያዎችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ወጥቷል፡፡

ደቡብ አፍሪካ በድምሩ አራት ፣  አልጀሪያ እና   ቡርኪናፋሶ እያንዳንዳቸው ሁለት  ሜዳሊያዎች በማግኘት ደረጃ ውስጥ መግባት እንደቻሉ ታውቋል፡፡

የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርዕስቱ ይርዳው በመዝጊያ ስነስርዓት ወቅት እንዳሉት የብስክሌት ውድድሩ እንደ ሃገርም ሆነ እንደ ክልል ተመሳሳይ ዝግጅቶችን ማስተናገድ እንደሚቻል የተረጋገጠበት ነው፡፡

በዚህ ውድድር ከትግራይ ክልል የመጡ ተሳታፊዎች የተሻለ ውጤት ማስገኘት እንደቻሉ ጠቅሰው ሌሎች ክልሎችም በዘርፉ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል፡፡

የአማራ ክልል ስፖርት ከሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ በበኩላቸው የክልሉ የፀጥታ ኃይል፡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና ማህበረሰቡ ባደረገው ጠንካራ ህብረት ውድድሩ በሰላም  መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴረሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ገዳ በበኩላቸው በውድድሩ ጠንካራ እንደነበር ገልፀው የሚጠበቀውን ውጤት ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ፡

ከሀገራቱ ከ100 በላይ ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና  ውድድር ሲጠናቀቅ ለአሸናፊዎቹ የሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም