የህክምና መሳሪያዎችን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

63

አዲስ አበባ  መጋቢት 10/2011ኢትዮጵያ ውስጥ የህክምና መሳሪያዎችን ለማምረት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈረመ።

ስምምነቱ የተፈረመው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እንደዚሁም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መካከል ነው።

ስምምነቱ ለህክምና መሳሪያዎችን ከውጭ ለማስገባት እየወጣ ያለውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስና የመሳሪያዎቹን አቅርቦት ለማሻሻል ያግዛል ተብሏል።

የጤና ሚንስቴር ዶክተር አሚር አማን ስምምነቱ ሲፈረም እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የህክምና መሳሪያዎችን ከውጭ ለማስገባት በየአመቱ ከአምስት ቢለዮን ብር በላይ ወጪ ታደርጋለች፤ ይህም ሆኖ በአገሪቱ ያለውን የህልምና መሳሪያ ፍላጎት ለማሟላት አልተቻለም። 

በአገሪቱ ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያም የሚፈለገውን ያህል መሳሪያ በሚፈለገው መጠን ከውጭ ማስገባው እንዳልተቻለም አክለዋል።

የህክምና መሳሪያዎችን በአገር ውስጥ በስፋት ለማምረት የሚያስችሉ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ማከናወን ከተቻለ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች በመቀነስ ተጨባጭ ለውጦች እንደሚመጡ እምነታቸውን ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተወሰኑ የህክምና መሳሪያዎችን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያስችል የፈጠራ፣ አቅም አና የቴከኖሎጂ ከህሎቶች ያላቸው ወጣቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከተቋማቱ ጋር የተደረገው ስምምነት የአገር ውስጥ ህክምና መሳሪያዎች በስፋት እንዲመረቱ ከማድረግ አንጻር ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑም አክለዋል።

የአገር ውስጥ ባለኃብቶች በህክምና መሳሪያዎች ምርት በስፋት እንዲሰማሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የንግድና ኢንደስትሪ ሚንስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሄር ናቸው።

ባለኃብቶቹ ደረጃቸውን የጠበቁ መሳሪያዎችን እንዲያመርቱና የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በበኩላቸው የጤናው ዘርፍ በስፋት ለማስደገፍ የሚያስችለው ኢንደስትሪ ፓርክ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአገር ውሰጥ ባለኃብቶችን ከውጭ ባለኃብቶች ጋር በማስተሳሰር በዘርፉ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የመደገፍ ስራ እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም