ለምርምር ማዕከል ግንባታ የለቀቅነው መሬት ለዓመታት ያለስራ በመቀመጡ ቅሬታ ፈጥሮብናል—የከጪ ወረዳ አርሶ አደሮች

505

ሶዶ  መጋቢት 10/2011 ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለምርምር ማዕከል ግንባታ የተረከበው ቦታ ያለሥራ ለስድስት ዓመት ታጥሮ በመቀመጡ አግባብ አይደለም ሲሉ በዳውሮ ዞን የከጪ ወረዳ አርሶ አደሮች ቅሬታቸውን ገለፁ።

አርሶ አደሮቹ ቅሬታቸውን የገለፁት ትላንት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ባካሄዱት የውይይት መድረክ ላይ ነው ።

“በማዕከሉ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ ተብለን ለግንባታው ከይዞታችን እንድንነሳ ቢደረግም ቦታው ያለጥቅም በመቀመጡ ቅሬታ አሳድሮብናል” ብለዋል አርሶ አደሮቹ ።

ዩኒቨርሲቲው ቅሬታውን በመቀበል በተረከበው ቦታ ላይ ማህብረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የተቀናጀ የምርምር ሥራ ለማከናወን ማቀዱን አስታውቋል ።

በውይይቱ ከተሳተፉ የወረዳው ነዋሪዎች መካከል  አርሶ አደር ስለሺ ሽፈራው እንደገለፁት በወቅቱ ከወረዳው አስተዳደር ጋር በተደረገ ውይይት ነዋሪው ልማቱ የኛው ነው በሚል ይገለገልበት የነበረውን መሬት ሰጥቷል ።

ማዕከሉ ለአካባቢው አርሶ አደር የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን በማቅረብ፣ በዘመናዊ ግብርና አሰራር የክህሎት ስልጠና በመስጠትና ከይዞታቸው ለሚነሱ የነዋሪ ልጆች የትምህርትና መሰል ድጋፎችን እንደሚሰጥ ተነግሯቸው እንደነበር አስታውሰዋል ።

“አልምተን እንጠቀምበት የነበረው መሬት ላለፉት ስድስት ዓመታት ምንም አይነት ሥራ ሳይካሄድበት ታጥሮ በመቀመጡና የተባለውንም ጥቅም ባለማግኘታችን ቅሬታ ፈጥሮብናል” ብለዋል።

” ማዕከሉ የነዋሪውን ሕይወት በዘላቂነት ይለውጣል በመባሉ ለስድስት ሄክታር ይዞታዬ ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቶኝ ከይዞታዬ ተነስቻለሁ ” ያሉት ደግሞ አርሶ አደር በለጠ ባተላ ናቸው።

በይዞታቸው ላይ ለነበሩ አራት መኖሪያ ቤቶች፣ ለተለያዩ የጓሮ አትክልቶችና ቋሚ ሰብሎች ካሳ ሳይጠይቁ በፍቃዳቸው ለልማት መነሳታቸውን አስታውሰዋል ።

ይገነባል የተባለው ማዕከል ባለመገንባቱና መሬቱ ያለጥቅም መቀመጡ ቅሬታ የፈጠረባቸው መሆኑንም አርሶ አደር በለጠ ገልጸዋል።

የከጪ ቱታ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታምራት ዘለቀ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በተደረሰ ስምምነት መሰረት በ2005 ዓ.ም 165 ሄክታር መሬት መረከቡን ተናግረዋል።

ከማዕከሉ ግንባታ ጋር ተያይዞ 24 አባወራ አርሶ አደሮች ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው ከይዞታቸው መነሳታቸውን አስታውሰዋል ።

በዩኒቨርሲቲው በሚቋቋመው ማዕከል በእንስሳት እርባታ፣ በተፈጥሮ ሀብትና በሰብል ልማት ላይ ያተኮሩ ምርምሮችን በማካሄድ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ  ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ ተግባራዊ ባለመሆኑ በነዋሪው ላይ ቅሬታ ማስነሳቱን ጠቁመዋል።

“ዩኒቨርሲቲው በጉዳዩ ላይ ከህዝቡ ጋር በመምከር የገባውን ቃል በቀጣይ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ በያዘው አቅጣጫ ላይ  ከህዝቡ ጋር ለመምከር የውይይት መድረኩ  ተዘጋጅቷል” ብለዋል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታከለ ታሰደ በበኩላቸው በተቋሙ የ100 ቀናት ዕቅድ ውስጥ የተያዙ ሰባት የምርምር ማዕከላትን በቴክኖሎጂ፣ በግብዓትና በሰው ኃይል የማደራጀትና የማጠናከር ሥራ ቅድሚያ የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል ።

የከጪ ምርምር ማዕከል የዕቅዱ አካል መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ በዕቅዱ መሰረት የተመራማሪዎች ማረፊያና የአገልግሎት መስጫ ግንባታዎች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።

በእንስሳት ሃብት ልማትና በንብ ማነብ ዘርፎች የምርምርና ማህበረሰብ አገልገሎት እንዲሁም ለአርሶ አደሩ የግብርና ክህሎት ሽግግር ተደራሽ የሚያደርጉ ሥራዎች እንደሚሰሩም አብስረዋል ።

በዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ አማካኝነት ማዕከሉን በአፋጣኝ ወደሥራ የሚያስገባ ኮሚቴ መቋቋሙንና ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንም አስታውቀዋል ።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ከይዞታቸው ለተነሱ አርሶ አደር ልጆች በጥናት ላይ የተመሰረተ የትምህርት፣ የሥራ ዕድልና ሌሎች ድጋፎች ይደረጋሉ።