ክለቡ ለተጫዋቾቹ 125 ሺህ ብር በስጦታ አበረከተ

68

ሆሳዕና መጋቢት 10/2011 የሀድያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ ለተጫዋቾቹ 125 ሺህ ብር በስጦታ አበረከተ፡፡

ክለቡ ስጦታውን ያበረከተው በአንደኛ ዙር ጨዋታ ክለቡ አንደኛ ሆኖ በማጠናቀቁ ነው፡፡

የሀድያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ማዶሬ እንደተናገሩት ክለቡ በአጠቃላይ 11 ጨዋታዎችን ተጫውቷል፡፡

በሰባት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በሦስት ጨዋታዎች አቻ መውጣቱንና በአንድ ጨዋታ መሸነፉን ተናግረዋል፡፡

ክለቡ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ከ "ሐ" ምድብ 24 ነጥብ በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃን መያዙን አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡

ተጫዋቾቹን ለማበረታት ክለቡ የገንዘብ ስጦታ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ክለቡ ለቀጣይ ምዕራፍ ዝግጁ ለመሆን ተጫዋች ከማሟላት ጀምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው፡፡

የክለቡ አምበል ትዕግስቱ አበራ በበኩሉ የክለቡ አባላት በቅንጅት በመስራታቸው ውጤት መመዝገቡን ለኢዜአ ተናግሯል።

" በቀጣይም ጠንክረን በመስራት የክለቡን ስም ለማስጠራት እንጫወጣለን ሲል" ተናግሯል።

በተደረገላቸው ማበረታቻ ደስተኛ መሆኑን የገለጸው የክለቡ አምበል ማበረታቸው በቀጣይም ውጤት እንዲያስመዘግቡ አደራ ጭምር የታከለበት መሆኑን ተናግሯል፡፡

"ከላይኛው የስፖርት አመራር ጀምሮ በቅንጅት መሰራቱ በአንደኛው ዙር የጨዋታ ውድድር አንደኛ እንድንወጣ ረድቶናል" ያለው ሌላው የክለቡ ተጫዋች ዮሴፍ ድንገቱ ነው።

የክለቡ ደጋዎች ማህበር አስተዋጽኦም ከፍተኛ መሆኑን አስታውሶ "ያመጣነው ውጤት የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ ባለመሆኑ የበለጠ መስራት ይጠበቅብናል" ብሏል፡፡

የሀድያ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሲሳይ እውነቱ በበኩላቸው ክለቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሻለና ውጤታማ እንዲሆን መምሪያው የሚጠበቅበትን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ክለቡ ዛሬ ባበረከተው ስጦታ ተጫዋቾቹ ከ1 ሺህ 500 እስከ 5ሺህ 000 ብር እንደተበረከተላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም