በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለው የጉልበት ሰራተኞች ዝውውር ህጋዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

73

መቀሌ መጋቢት 10/2011 በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለው የጉልበት ሰራተኞች ዝውውር ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖራው ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት ለማሰባሰብ የሁለቱም ሀገራት ተወካዮች የተካፈሉበት የምክክር መድረክ በመቀሌ ከተማ ተካሄዷል፡፡

ከመድረኩ ተካፋዮች መካከል በኢትዮጵያ ስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የየብስ ኬላዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ግርማይ የማነ  እንደገለጹት የምክክር መድረኩ በሁለቱም ሀገራት በኩል የህግ ማዕቀፎች ለማውጣት የተዘጋጀ ነው፡፡

ይህም የሚከናወነው የተባበሩት መንግስታት የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብትና አፍሪካ በ2063 አንድ የጋራ ማህበረሰብ ለመመስረት የተያዘው ራዕይ በማይጻረር መልኩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ 

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የስነ ህዝብ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ክንፈ አብርሃ በበኩላቸው " በሁለቱም ሀገራት ያለው የሰዎች ዝውውር ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ እንቅስቃሴ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል "ብለዋል፡፡

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀውም ዝውውሩ ህጋዊ ማዕቀፍ  እንዲኖራው ፖሊሲ  አውጪዎች  መረጃ ላይ ተመስርተው ህግ እንዲያወጡ የሚያግዝ ግብአት ለማሰባሳብ  መሆኑን አስረድተዋል፡፡

"በሁለቱም ሀገራት  የሚካሄደው የጉልበት ሰራተኞች ዝውውር ከግለሰቦች አልፎ ለሀገራቱ ግንኙነት  መጠናከር የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል" ብለዋል።

ለጉልበት ስራ ወደ ሁለቱም ሀገራት  የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚያከናወኑትን በግልፅ እንዲለይ በማድረግ ኃላፊነታቸው እንደወጡና መብታቸው እንዲከበር የሚያግዝ ጥናት በኢትዮጵያ የመቀሌ እና በሱዳን ደግሞ የገዳሪፍ ዩኒቨርስቲዎች  ማካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ  ሀገራት  ከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት በዚሁ ዙሪያ  መስራት እንደሚኖርባቸው ያመለከቱት ደግሞ የገዳሪፍ ዩኒቨርስቲ  ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ኢብራሂም ዓብዱሰላም  ናቸው፡፡

የሁለቱ ሀገራት ዜጎች ለዘመናት  በራሳቸው  በፈጠሩት ግንኙነት እንደ አንድ ቤተሰብ አብረው እየሰሩ መሆኑን  ገልጸው " እንደ ትምህርት ተቋማት መብታቸው ምን ያህል እየተከበረ መሆኑን አንስተን ማጥናትና በዘርፉ ላይ ምርምር ማካሄድ ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡

ለጉልበት ስራ የሚንቀሳቀሱ ከህገወጦች  በመለየት የጤና አገልግሎትና ሌሎች ጥቅሞች የሚያገኙበት አሰራር  ሊፈጠርላቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በባህርዳር ዩኒቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ ፋካሊቲ ዲን ዶክተር ቃለ ወንጌል ምናለ በበኩላቸው  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ለምን እንደሚደረግ ፋይዳውን  በማየት  ችግሮችን በሚፈታ መልኩ ምርምር ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

" የጉልበት ሰራተኞች ዝውውር ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲይዝ ማድረግ በሁለት ሀገራት መካከል የሚደረጉ የምክክር መደረኮች በአጎራባች ህዝቦች መካከል ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶችም ለመከላከል ያስችላል "ብለዋል።

ከሱዳን ገዳሪፍ ክፍለ ሀገር ከመጡት አርሶአደሮች መካከል ያሲር ዓሊ በሰጡት አስተያየት በአጎራባች ካሉት ኢትዮጵያዊያን  አርሶ አደሮች ጋር ያላቸው ግንኙነት ለዘመናት የቆየና ወደ ወንድማዊነት የተሸጋገረ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰዎች ዝውውር ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው ማድረግ በሁለቱም ሀገራት ድንበር አካባቢ የሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለማጠናከር ይረዳል፤ በዚህ ስራ የሚሰማሩ ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ  ነው ተብሏል፡፡

በመቀሌ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የምክክር መድረኩ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም