ቅንጡው ርእሰ ጠበብት- 'አፈወርቅ ወልደ ነጎድጓድ'

256

አየለ ያረጋል (ኢዜአ)

አገር፤ ኩባንያ አይደሉም፤ ሰዓሊ ግለሰብ እንጂ። ሰዓሊው ግን እንደ ተቋም የራሳቸውን ዓርማ ሸራው ላይ ፈጥረዋል። ለራሳቸው ሥያሜ ሰጥተዋል። የስዕል ጠቢቡ ራሳቸውን 'አፈወርቅ ወልደነጎድጓድ' (Alpha Son of Thunder) ብለዋል። ከአፈወርቅ ተክሌነት ይልቅ 'አፈወርቅ ወልደ ነጎድጓድ' ከተንቀሳቃሽ መኪና እስከ ቅንጡ ቪላ ግድግዳቸው ላይ በደማቅ ጽፈዋል። ርእሰ ጠበበት አፈወርቅ በጥበብ ልቀት 'በዓለም ላይ' ራሳቸውን "እጅግ" አስከብረዋል።ጥበቡ ከምድር አድማስ ተሻግሮ ጨረቃ ላይ ማማ ቀልሷል። የቅርብ ጓደኛቸው ገጣሚና ፀሃፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ለስዕል ጠቢቡ 'እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲሰት አፈወርቅ ተክሌ' አድናቆቱን እንዲህ ገልፆላቸዋል።

"እግዚአብሔር አርቲስቱን ፈጠረ

አርቲስቱ ቀለማትን ቀመረ

ከዚያም ሸራውን ወጠረ

ተፈጥሮን ደግሞ ፈጠረ

ሰውን ደግሞ ፈጠረ

ኩራተ ርዕሱንም ፈጠረ

እውነትም አፈወርቅ ትንሽ ፈጣሪ ነበረ

አልፋ ኦሜጋም ነበረ"

አፈወርቅ በሸዋ ነገሥታት አምባዋ አንኮበር ከአቶ ከተክሌ ማሞና ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ በ1925 ዓ.ም ነበር የተወለዱት። ጨቅላነታቸው በፋሺስት የግፍ ወረራና ጦርነት በሰው፣ በንብረትና ባህል ጥፋት ዘመን ነበር። በ15 ዓመት እድሜያቸው እንግሊዝ ተሻግረው በአዳሪ ትምህርት ቤት በሒሳብ፣ ኬሚስትሪና ታሪክ ድንቅ ውጤት አምጥተዋል። በሎንዶን የኪነ ጥበብ ማእከላዊ ትምሕርት ቤት፣ በኋላም በስመ ጥሩ የሎንዶን ዩኒቨርሲቲ የስሌድ ኪነ ጥበብ አካዳሚ ፈር ቀዳጁ አፍሪካዊ ደቀ መዝሙር ናቸው። በስዕል፣ በቅርጽና በኪነ ሕንፃ ዕውቀት ገብይተዋል። በእንግሊዝ አገር በገበዩት ዕውቀት ብቻ ግን አልተገደቡም።

ኢትዮጵያ ተመልሰው ኢትዮጵያን፤ ታሪኳን፣ ባህልና ወጓን ተዘዋውረው አጥንተዋል። በውጭ ባህልና ወግ ቢማሩም ከኩረጃ ይልቅ ራስን መሆን በሚል ፍልስፍና ጸንተዋል። “ምኞቴ በዓለም የታወቀ ኢትዮጵያዊ የኪነ ጥበብ ምሑር መሆን ስለነበር፣ የአገሬን ወግና ባሕል ጠንቅቄ ማወቅና ማጥናት እንዳለብኝ አውቄያለሁ። ሥራዬ የዓለም ንብረት ይሆናል ነገር ግን በአፍሪቃዊነት ቅመም የጣፈጠ ሥራ ነው የሚሆነው” በማለት ብዙ ደክመዋል። ድካማቸው ፍሬ አፍርቷል። ዓለም አቀፋዊ ክብርና ዝና የተጎናጸፉ፣ 'እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ' የተባሉ ኢትዮጵያን ያስጠሩ ኩሩ የሥነ ጥበብ ሰው ሆነዋል።

ኪነ ጥበብ ለኅብረተሰባዊ መሳሪያ በሚለው መርሃቸው ጸንተዋል። ለዚህም ይመስላል ኪነ ጥበብን ሚና ''ኪነ ጥበብ የሰው ልጅን መንፈስ ለማዳበር፣ ሀገራችንን ለማሳደግ፣ ለማሳወቅ እና ለሕይወታዊ ኑሮ ተስፋ ለመፍጠር የላቀ ሚናይጫወታል’። ዛሬ የምንሠራው ሥራ የዛሬን ሕይወት እያንጸባረቀ ለነገው ትውልድ ፈር መቅደድ አለበት” ሲሉ የተናገሩት። ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እስከ እሰከ ኃያላን አገራት መድረኮች የጥበብ ትርዒት አቅረበዋል። ኢጣልያ፣ ፈረንሳይ፣ እስፔይን፣ ፖርቱጋል፣ እንግሊዝ፣ ግሪክ አገሮች የጠለቀ የኪነ ጥበብ ጥናት አድርገዋል። ከአሜሪካ አስከ ሩስያ በክብር ተጠርተው ሰርተዋል። የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት በጥልቅ አጥንተዋል። በመስታወት ቅብ ስዕል (stained glass art) እና የ’ሞዜይክ’ አሠራርን ጥበብ ተራቀዋል።በቴምብር ስዕላት ገነዋል። “የእኔን ሥራ የሚያዩ ሁሉ ተስፋ እንዲያገኙ፣ ስለኢትዮጵያና ስለ አፍሪቃ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው፣ በፀሐይ ጮራ እንዲሞቁ፣ ከሁሉም በላይ ግን 'ይቻላል' የሚል እምነት እንዲኖራቸው ፍላጎቴ ነው” በለዋል ስለኪነ ጥበብ ስራቸው። በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ መግቢያ ላይ ‹‹አፍሪካ ያኔ፣ አፍሪካ አሁን እና አፍሪካ ወደፊት›› የሚለው የመስታወት ላይ ሥራቸው ዓለም አቀፋዊም አድናቆት አስገኝል። የቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ ሽልማት ድርጅት ቀው የስነ ጥበብ ተሸላሚ ብቻ ሳይሆን ''ወርልድ ሜዳል ኦፍ ፍሪደም'' የተሰኘው ሽልማት ተጎናጽፈዋል፡፡  

ዓለም ያከበራቸውን ርእሰ ጠበብት አፈወርቅ ወልደ ነጎድጓድ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ኢትዮጵያ መታሰቢያ ሐውልት አላቆመችላቸውም። መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ የሚገኘው የመቃብር ሐውልታቸውም(ከነሚሰነዘርበት ትችት) ከሞቱ ከአራት ዓመት በኋላ ነው የቆመላቸው። የእርሳቸው ብቸኛ መታሰቢያ ስራቸውና ቅንጡ 'ቪላ አልፋ'ቸው ነው። ይህን ቅንጡ ቪላቸው በሕይወት እያሉ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ አውርሰዋል።ይህ ቅንጡ ቪላቸው ምን ላይ ይገኛል።

ቪላ አልፋ

አፈወርቅ ወልደ ነጎድገድ ኑሯቸውን በስርዓት ኖረዋል። ይህን ለመገመት 'ቪላ አልፋ'ን መጎብኘት ይበቃል። ዘመነኞቹ ቢሳለቁባቸውም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት 'ቅንጡ ቪላ' ገንብተው ብዙ ተብሎላቸዋል። የአፈወርቅ 'ቪላ አልፋ' በኢትዮጵያ እንግዳ ክስተት ነበር። ቅንጡዎች ለግላዊ መኖሪያ ቅንጡ ግቢ ሲገነቡ 'ቪላ አልፋ' ብለው ይጠሩታል። አፈወርቅም 'ቪላ አልፋውን ለመገንባት ከስዕሎቹ ሲሶውን ቆጥበዋል። ዳሩ ያጠራቀሙት ጥሪት የቪላ አልፋን ወጭ አልሸፈነምና እጃቸውን ወደ ባንክ ዘረጉ። ጠቢባን በድህነት በሚኖሩባት ኢትዮጵያ ቅንጡው ርእሰ ጠበብት ግን ቅንጡ 'ቪላ አልፋቸውን' አዲስ አበባ ላይ ገተሩ። ቪላው ግን ዝም ቪላ አይደለም። ይህ ቅንጡ የመኖሪያና የጥበብ ስራ ማዕከል የጊዜና ቦታ አጠቃቀምን፣ የአገር ፍቅርን፣ ኪነ ጥበብን ያስተማረበት፣ ራስን፣ ሙያን ማክበርና መውደድን ያሳየበት፤ የጥበብ ምንጭ የፈለቀበት፣ ጥሪቱን ያፈሰሰበት ግቢው ነው።

አንጋፋውና ስመ ጥሩው የሙዚቃ ሰው ሙላቱ አስታጥቄ ስለ አፈወርቅና ሰለ ቪላ አልፋ በአንድ ወቅት "አፈወርቅ በእውነት የሚደንቅ ሰው ነው፡፡ አልፎ አልፎ እንገናኝ ነበር፡፡ ቤቱን (ቪላ አልፋ) ለመጎብኘት ሄጄ ያየኋቸው ሽልማቶች ስመለከት፣ ለአንድ አፍሪካዊ ሠዓሊ በዓለም ዙርያ ይህ ሁሉ ክብር ተሰጥቶት ሳይ በጣም ነው ያኮራኝ፡፡ ወጣቶቹ በተለይ ቪላ አልፋ በሚከፈትበት ሰዓት ላይ እነዚያን ሽልማቶች መመልከትና መመራመር ከቻሉ እነርሱም እንደሱ መሆን እንዲችሉ ያነሳሳቸዋል" ብለው ነበር፡፡

ዝነኛው ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ በ1961 ዓ.ም በጊዜው በሰዓሊው ቅንጡ 'ቪላ አልፋ' መልክ ስለሚናፈሰው ወሬ ፅፎ ነበር። ሰዓሊው በወቅቱ ስለሚሰነዘርባቸው የተለያዬ ትችት ለጋዜጠኛው “ተርፎት፣ የሚሠራውን ቢያጣ ለመመጻደቅ ያደረገው ነገር ነው” ሲሉ መልሰዋል። "ጐንደር የሚገኘውን የአፄ ፋሲልን ግንብ የሚመስል ባለአንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት ባለንበት ክፍለ ዘመን በመሥራቱ ነው ልዩው ነገር። ሌላ ሰው ቢያስብም ሥራ ላይ የማያውለውን ነገር አፈወርቅ ግን በመሥራቱ ነው" ብሏል ጋዜጠኛው። "ከአፈወርቅ በስተቀር እንዲህ የመሰለውን ቤት አልሞ የሚሰራ የለም። የሚሰጠውን ጥቅምም በይበልጥ የሚያውቀው እሱው ብቻ ነው" እያለ ይቀጥላል። ለቃለ መጠይቅ በስፍራው በተገኘበት ወቅት ትዝብቱን እንደጻፈው እያንዳንዱ የግንባታና የግቢ አደረጃጅት በትርጉምና በምክንያት(በሰዓሊው ንድፍ) ስለሚደረግ 'አናጢዎቹና ሰራተኞቹ    በየደቂቃው ይጠሩታል" ብሏል። አፈወርቅን ሳያማክሩ መስራት እንደማይቻል ትዝብቱን ከትቧል። ሰዓሊውም “ማንኛውም ነገር ከተፈጥሮ ጋር በመዋሀድ በኅብረ ቀለሙና በአቀማመጥ አቅዱ ለአእምሮ ዕረፍትና ሰላምን ካልሰጠ አእምሯችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚመራ ነገር የመፍጠር ችሎታ ሊኖረው አይችልም። ከተፈጥሮ ኅብረት ጋር ሥራችንንና ኑሯችንን ለማስተባበር ካልሞከርን ውበትን ለመፍጠር አንችልም።ለኔ ከፍተኛው ምኞቴ ይህ ነው – ኅብረት ከተፈጥሮ ጋር። ይህንን ከፍተኛ ምኞት ለመግለፅ የምፈልገው በምሠራቸው ሥዕሎች ብቻ ሳይሆን በአኗኗሬም ጭምር ነው” ብለውታል። ቀጥሎም 'ይህን ቤት መሥራት ከጀመርኩ ወዲህ የተማርኩት ነገር ቢኖር የቤት ሥራ ምን ያህል ብስጭትና ድካም እንደሚያስከትል ለማወቅ መቻሌን ነው። ወደ ሰላማዊው የሥዕል ሥራዬ የምመለስበት ጊዜ በመቃረቡ ደስ ይለኛል' አለና እግሩን ዘርግቶ ወለሉ ላይ ዘፍ አለ" ይላል በዓሉ ግርማ።

ቪላው በ2 ወራት ለማጠናቀቅ ቢታቀድም ከታቀደለት ጊዜ እጥፍ በላይ ወስዷል። ሰዓሊው በቤቱ ስራ በመወጠሩ በአራት ራት ውስጥ አፈወርቅ ሦስት ሥዕሎች ብቻ መስራቱን ይገልጻል። “ቪላ አልፋ” የተሠራው በአሥር ዓመት ፕላን መሠረት ነው።አፈወርቅ ከሚሸጣቸው ሥዕሎች ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ለዚህ ፕላን ቆጥቧል። ሆኖም የቆጠበው ገንዘብ ስላልበቃው የአዲስ አበባ ባንክ ብድር ሰጥቶታል። '26 በ26 ሜትር ካሬ መሬት ላይ የተሠራው ቪላ “ስለ አፄ ፋሲል ግንብ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽና ይህ የጥንት ቅርሳችን ተሻሽሎ ለዘመናይ ኑሮ ለመዋል መቻሉን ለማሳወቅ ነው። አዎን የኮራና የከበረ ቅርስ እያለን የቤት ፕላን ከውጭ የምንቀዳበት ምክንያት አይታየኝም” በማለት የኢትዮጵያን ኪነ ህንጻ ጥበብ መምረጣቸውን ተናግረዋል።

"አፈወርቅ ለሚሠራው ነገር ሁሉ ምክንያት አለው" ይላል በዓሉ። 'ቤቱ አንድ ሺህ ሜትር ካሬ ላይ መሠራቱ ምክንያት አለው። የመሬት ቁጠባን ለማስተማር ነው። በቤቱ ውስጥ ያለ ምክንያት የሚደረግ ነገር የለም። የአበባ ማስቀመጫው፣ የቤቱ ቆርቆሮ ቀይ ቀለምና የግድግዳው ነጭ ቀለም ምክንያት አለው። ቤቱም ቀለሙም አቀማመጡም – ሁሉም ባንድነት ተዋህደው ኅብረት መፍጠር አለባቸው' እያለ ይተርካል። “አንድ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ እንዴት እንደሚኖር ለማሳየትና ከዚህም አልፎ ከሀገራችን የታሪክ ቅርስ ጋር ለማስተዋወቅ ነው። እንግዶቼ በውብ ነገር ተከበው ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ ሌላ የዕለት ኑሮዬን እንዴት እንደማሳልፍ እንዲያውቁም ጭምር ነው። ከዚህ ቀደም ቤቴ በግንብ አጥር ተከቦ ታፍኜ ስኖር ነበር። አሁን ግን የቤቱ ሰገነት ወደ ውጭና ወደ እሩቅ ለመመልከት ያስችለኛል። ሰገነቱ ላይ ወጥቼ የአዲስ አበባ ተራራዎችን ለማየት እችላለሁ። ላንድ ሠዓሊ እንዲህ ያለው የመዝናናት ትዕይንት ጠቃሚው ነው።” ብለዋል።

''የቤቱ ክፍሎች አቀያየስ ምክንያት አላቸው። ሃምሳ አራት ሥዕሎች ባንድ ጊዜ ለማሳየት እንዲቻል ታስቦ የተደረገ ነገር ነው። እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍል ከየጠቅላይ ግዛቶች የሚገኙትን ጌጣጌጦች ማሳያ ሊሆን ይችላል። የጸሎት ወይም የሀሳብ ማጠንጠኛ ክፍሉ የአክሱም ጽዮንን መልክ የያዘ ነው። የምሥጢር በሩ ያለ ምክንያት አልተሠራም። አፈወርቅ ካንዱ ክፍል ወደ ሌላ ሳይታይ ለመዘዋወር እንዲችል ነው። የጋራጁም ስፋትና ቀለም ያለ ምክንያት አልተደረገም። ሁለት መኪናዎች እንዲይዝ ከመሆኑም በላይ የጋራጁ ቀለም ከመኪናዎቹ ቀለም ጋር ተዋህዶ ኅብረትን ለመፍጠር እንዲችል ታስቦ ነው። አዎን፣ በአፈወርቅ ቤት ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም" የበዓሉ ግርማ ብዕር ነው።

የስነ ጥበብ ስራ ቦታና መኖሪያ የነበረው 'ቪላ አልፋ' ዕድሳት ላይ ይገኛል። እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወረቅ ተክሌ ጦር ኃይሎች አካባቢ የሚገኘውን 'ቪላ አልፋ' የተሰኘውን የመኖሪያና የስዕል ጋለሪ ግቢ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ እንዲተላለፍ ከሕልፈታቸው በፊት በተናዘዙት መሰረት ታድሶ ለስነ ጥበብ ቤተ መዘከርነት ያገለግላል።

ትናንት መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም የባህል ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው የተመራ ቡድን የእድሳቱን ሂደት ተመልክቶ ነበር። በ1961 ዓ.ም የተገነባው ቪላ አልፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕንጻ ጥበብ ኮሌጅ አማካሪነትና የሻርፕ ኢንጂነሪንግ ኤንደ ሲስተም ሶሉሽን በተባለ ተቋራጭ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ባለቤትነት ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ ዕድሳቱ እየተካሄደ ነው። 

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የብሔራዊ ቤተ መዘክር ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ አርቲስቱ ከሞቱ በኋላ በቤተሰባቸው "ይገባኛል" ጥያቄ ለብዙ ጊዜ በሕግ ጉዳይ ተይዞ የነበረውን 'ቪላ አልፋ' በፍጥነት አድሶ ለጎብኝዎች ክፍት ማድረግ አለመቻሉን ይናገራሉ። በአዲስ አበባ ፖሊስ ጥበቃ እየተደረገለት ቆይቶ የፍርድ ሂደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ፤ የባለሙያዎች ኮሚቴ ተዋቅሮ ተገቢው የስዕልና ግል ንብረት ቆጠራና ምዝገባ ስራዎች ተከናውኗል። 'ቪላ አልፋ' ሲታደስም የሰዓሊው የጥበብ ስራዎች ቀድሞ በተደራጁበት መልኩ ካለምንም መዛነፍ እንዲቀመጡ ለማድረግ የቆጠራና የምዝገባ ስራው ረጂም ጊዜ መውሰዱንም ይናገራሉ።

ከምዝገባና ቆጠራ በኋላም እድሳቱ እስኪጠናቀቅ በቪላው ውስጥ የተገኙ ከ440 በላይ የሚሆኑ ስዕላት፣ፎቶዎች፣መጻሕፍት፣ የወግና የመገልገያ ቁሳቁሶችና ንብረቶች ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ በጊዜያዊ ክፍል ተቀምጠዋል። አፈወርቅ ወልደነጎድጓድ በልዩ ጥበብ ሰርተው የሚለብሷቸው የክብር ቅንጡ አልባሳትምም ለዓመታት በባዶ ቤት ተቀምጠዋል። ዕድሳቱን የሚያከናውነው ተቋራጭ ተወካይ አቶ ሸምሰዲን ዳውድ እንዳሉት ስዕላቱም ሆነ ሌሎች ንብረቶች ሳይጎዱ በጥንቃቄ ማቆያ ክፍሎች ተሰርተውለት ነው እድሳቱ እየተደረገ ያለው። ጣራና ኮርኔሱ ተጎድቶ በማፍሰሱ የውስጥ ግድግዳዎች ተጎድተው እንደነበር አቶ ሸምሰዲን ይናገራል። እድሳቱም ከጣራ እስከ ግድግዳ ያሉ ስራዎችን የሰዓሊውን ቀደምት የአሰራር ጥበብ ተከትለው የታደሱን ነው ናት። ቀለም ቀቢዎችም ተራ ቀለም ቀቢዎች ሳይሆኑ የስዕልን ጥበብ የሚያውቁ ሰዓሊዎች ናቸው ይላል። አሁን ላይ ከተወሰኑ ክፍሎች በስተቀር የቪላው ውስጣዊ ክፍሎች አጠቃላይ የእድሳት ስራዎች ተጠናቀዋል። በመጭው  ሰኔ በሚጠናቀቀው የእድሳት ውል መሰረት ተቋራጩ ቀሪ ስራዎችን አከናውኖ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ሰርቶ እንደሚያስረክብ አረጋግጠዋል።

የዕድሳት ሂደቱን የተመለኩት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በልዩ የቤት አሰራር ጥበብ የተገነባውና በስዕላት ጥበብ ያሸበረቀው የሰዓሊው መኖሪያ ግቢ፤ የአርቲስቱን የጥበብ ፍልስፍና የሚዘክር ግቢ ነው ይላሉ። "ቪላ አልፋ ለኢትዮጵያዊያን ብዙ ትምህርት ያስተምራል" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሙያን ማክበር፤ ራስን የመምራትና በስርዓት የመኖርን ምስጢር የሚያስተምር ተቋም ይሆናል ብለዋል። ግቢው የሙያ ብቻ ሳይሆን ለልጆች ትልቅ የሰብዕና መገንቢያ ተቋም እንደሚሆን እምነትቸው ነው።

ዕድሳቱን በማጠናቀቅም ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በጥበብ ቤተ መዘክርነት ለጎብኝዎች ክፍት ይደረጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም