የመኢአድ አመራሮች በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በመፍታት በጋራ ለመስራት ተስማሙ

88

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2011 የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አመራሮች  በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በመፍታት በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገለጹ።

በፓርቲው አባላት መካከል የተደረገውን ዕርቀ-ሰላም በማስመልከት የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በፓርቲው አመራሮች ዘንድ በመርህ ላይ በነበረው አለመግባባት ላለፉት 8 ዓመታት ራሳቸውን ከፓርቲው አግልለው ከቆዩ አመራሮች ጋር በተደረገ ሰፊ ውይይት መስማማት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።

የመኢአድ ሊቀ-መንበር ዶክተር በዛብህ ደምሴ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ፓርቲውን በመምራት ላይ ያለው አመራር አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ በማዋቅር ችግሩን ለመፍታት ሰፊ ጥረት በማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

በስምምነቱም ከዚህ በፊት በፓርቲው በነበረውን የአቋም ልዩነት ከድርጅቱ ራሳቸውን አርቀው የቆዩ አመራሮችና አባላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለሱ መወሰኑን ገልጸዋል።

በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የተደረሰውን ስምምነት በመረዳት ያላቸውን ልዩነት በመተው ከፓርቲው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። 

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለተገኘው ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከነበራቸው አመራሮች ጋር የተደረሰው ስምምነት በቀጣይ ፓርቲው ለሚያደርገው ሰላማዊ ትግል ወሳኝ መሆኑን ዶክተር በዛብህ ተናግረዋል።

የቀድሞ የፓርቲው ሊቀ-መንበር እና በተደረገው ዕርቀ-ሰላም ፓርቲውን የተቀላቀሉት አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተናጥል ሳይሆን በጋራ የሚሰራ የተባበረ ክንድ ያስፈልጋል።

በፓርቲው አመራሮች መካከል የተደረገው ዕርቀ-ሰላም ልዩነትን አቻችሎ በጋራ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ስራ ለመስራት የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በ1984 ዓ.ም በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የተመሰረተ ፓርቲ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም