የሰመራ - ሎግያ ከተማ ወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ችግራቸው እንዲፈታላቸው ጠየቁ

63

ሰመራ  መጋቢት 10/2011 በአፋር ክልል የሰመራ - ሎግያ ከተማ ወጣቶች ያለባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ችግር እንዲፈታላቸው ጠየቁ።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በበኩሉ የማዘውተሪያ ቦታ ችግሮችን ለመፍታት ከከተማ መስተዳድሩ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

የሎግያ ከተማ ነዋሪ ወጣት አብዱ ያሲን እንዳለው በከተማው ውድድር ለማካሄድም ሆነ ወጣቶች በየአካባቢያቸው የሚጠቀሙባቸው ምንም አይነት የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች የሉም።

በመሆኑም ወጣቶች ለስፖርቱ ምቹ ባልሆኑ የትምህርት ቤት ሜዳዎችና በግለሰብ ይዞታ ስር በሚገኙ ቦዶ ቦታዎች ላይ በመሄድ ለመጠቀም እየተገደዱ መሆናቸውን ገልጿል።

ወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ በአቅራቢያቸው አለማግኘት ከስፖርቱ እንዲርቁና ለተለያዩ ደባል ሱሶች እንዲጋለጡ ያደረጋቸው በመሆኑ መንግስት ችግሩን እዲፈታላቻው ጠይቋል።

ሌላው የሰመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት መሀመድ ሰኢድ ከተማዋ 15 ዓመት ዕድሜ ብታስቆጥርም የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች በማስተር ፕላን ባለመካተታቸው እየተቸገሩ መሆናቸውን ተናግሯል።

በከተማው ለእግር ኳስም ሆነ ለተለያዩ ስፖርቶች ይጠቀሙበት ለነበረው ሜዳ ምትክ ሳይዘጋጅ ለአረንጓዴ ልማት እንዲውል መደረጉ በተለይ በስፖርት ማደግ የሚፈልጉ ልጆችን ተስፋ ማስቆረጡን አመልክቷል።

አዳዲስ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በየአካባቢው የሚዘጋጁ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ገልጾ የክልሉ መንግስት ተገቢ ትኩረት በመስጠት የስፖርት ሜዳዎችን እንዲያስፋፋ ጠይቋል።

የአፋር ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱ ሀሰን በበኩላቸው በክልሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ችግር መኖሩን አምነው በየአካባቢው ወጣቶች ሲያዘወትሩባቸው የነበሩ ሜዳዎች ለሌሎች አገልግቶች እዲውሉ መደረጉን ለችግሩ መከሰት ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

"በክልሉ ከ300 በላይ ጥርጊያ ሜዳዎች ቢገኙም የባለቤትነት ይዞታ ማረጋጋጫ ያላቸው ሜዳዎች ከ40 የማይበልጡ ናቸው" ብለዋል።

"በወረዳ ደረጃ ስፖርት የራሱ አደረጃጃት አለመኖሩ ስራውን በባለቤትነት ሊሰራ የሚችል አካል እንዳይኖር አድርጓል።" ያሉት አቶ አብዱ፣ የአደረጃጀት ችግሩን ለመፍታት በቅርቡ በተጀመረው የሪፎርም ሥራ ተካቶ እንዲሰራ መደረጉን ገልጸዋል።

በሰመራ ከተማ ያለውን የስፖርት ማዘውተሪያ ችግር ለመፍታት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅርበት በመወያየት በየቀጠናው ለእግር ኳስ፣ መረብ ኳስና ቅርጫት ኳስ ሜዳዎች የሚያገለግሉ ጥርጊያ ሜዳዎችን ለማዘጋጀት መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ በሎግያ ከተማ ያለውን የማዘውተሪያ ቦታ ችግርም ለመፍታት በቅርቡ ከከተማ አሰተዳደሩ ቦታ መረከባቸውንና በተያዘው ዓመት መጨረሻ ድረስ የሜዳው ዝግጅት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም