4ተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ እንዲራዘም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ትክክለኛ ነው ---አብን

67

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2011 በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ካለው አለመረጋጋትና ከፍተኛ የዜጎች መፈናቀል አንጻር 4ተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ እንዲራዘም የቀረበው ውሳኔ ሃሳብ ትክክለኛ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ገለጸ።

በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወገኖች ወደ ነበሩበት ቀዬ የመመለሱ ስራ በበቂ ሁኔታ ባለመሰራቱ 4ኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ እንዲራዘም የቆጠራ ኮሚሽኑ ባካሄደው ስብሰባ ውሳኔ አስተላልፏል።

ይህንንም ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ዛሬ በሰጠው መግለጫ የቆጠራው ጊዜ እንዲራዘም ኮሚሽኑ ያቀረበው ሃሳብ "ትክክለኛና የህዝቡንና የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው" ብሏል።

የድርጅቱ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ መልካሙ ሹምዬ እንደገለጹት፤ በአገሪቷ በአሁኑ ወቅት ያለው የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የዜጎች መፈናቀል ባለበት ሁኔታ የህዝብና ቤት ቆጠራን ማካሄድ ተገቢ አለመሆኑን ድርጅቱ ያምናል።

እነዚህ አለመረጋጋቶች ባሉበት ሁኔታ ቆጠራውን ማካሄድ ትክክለኛ የሆነ መረጃ እንዳይገኝና ጥያቄዎች እንዲነሱ የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር የዜጎችንና የክልሎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያዛባ ስለመሆኑም እንዲሁ።

በዚህም ድርጅቱ የህዝብና ቤት ቆጠራው ከመካሄዱ አስቀድሞ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች እንዲስተካከሉና ቆጠራው እንዲራዘም በተለያዩ ጊዜያቶች ለሚመለከተው አካል ሲጠይቅ ቆይቷል።

በተለይም በአገሪቱ ካለው መዋቅራዊና ወቅታዊ ችግሮችን ጨምሮ የህግ-ማዕቀፍ፣ የተቋማት አደረጃጀት፣ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትና ሌሎችም ጉዳዮች በትኩረት እንዲቃኙና ቆጠራው እንዲራዘም ፍላጎቱን ሲያሳይ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በዚህም ፍትሃዊና ጥያቄዎችን የማያስነሱ ጉዳዮችን አስቀድሞ በመፍታት፣ የአገሪቷን የጸጥታ ሁኔታ በመገንዘብ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ካለው የህዝቦች መፈናቀል አንጻር መዋቅራዊ መሻሻያዎች የሚያስፈልጋቸውን ማስተካከል ተገቢ ነውም ብለዋል።

በሌላ በኩል ድርጅቱ በአገሪቷ የሚፈናቀሉ ዜጎችን መንግስት የዜጎችን እኩልነት በማረጋገጥ፣ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ በማድረግ፣ ወደቀያቸው በማቋቋም፣ በመመለስ ህጋዊ ከለላ በመስጠት ግዴታውን ሊወጣ ይገባልም ብሏል።

4ተኛው ህዝብና ቤት ቆጠራ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ተገልጾ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ይሁንና የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽኑ የውሳኔ ሃሳቡን ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እንዲቀርብ በአብላጫ ድምፅ መወሰኑን ተከትሎ ቆጠራው እንደሚራዘም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም