የምርምር ውጤቶች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ መስራት ይገባል...ምሁራን

77

ጎባ መጋቢት 10/2011 በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የምርምር ውጤቶች ሥራ ላይ ውለው ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ለተግባራዊነታቸው ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ምሁሯን ገለጹ።

"በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት ፍትሃዊነት በሕብረተሰብ ጤና ምርምሮች ማጎልበት !" በሚል መሪ ሀሳብ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ትናንት ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት የአውደ ጥናቱ ተሳታፊ ምሁሯን እንደገለጹት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚካሄዱ የምርምር ውጤቶች ሥራ ላይ ውለው የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በመፍታት በኩል ክፍተት ይታይባቸዋል።

በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ማምህር አቶ ስንታየሁ ኃይሉ በባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በወላድ እናቶችና ህጻናት ላይ በሚታዩ የምግብ እጥረት ችግሮችና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በጥናት ግኝታቸው መሰረት 30 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትና ወላድ እናቶች ለምግብ እጥረት ችግር መጋለጣቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ጥናት ብቻውን በራሱ ግብ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ስንታየሁ መንግስት የጥናት ውጤቱን ተግባራዊ በማድረግ ችግሩ የሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ከዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ጥናት ያቀረቡት አቶ ከድር ሁሴንበበኩላቸው ምርምሮች ከተጠኑ በኋላ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በታዋቂ ጆርናሎች ላይ ቢታተሙም የህብረተሰቡን ችግር እንዲፈቱ ወደመሬት በማውረድ በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ከድር እንዳሉት ምርምሮችን ወደ ፕሮጀክት በመቀየር ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የጥናት ግኝቶችን በአካባቢው ቋንቋ በመተርጎም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ማድረስ ያስፈልጋል፡፡

በሀገሪቱ የጤና ተቋማትን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ በኩል መሻሻሎች ቢታዩም  በጤና ተቋማት ውስጥ በተለይ ለወላድ እናቶች የሚደረገው እንክብካቤ ላይ ውስንነቶች እንደሚታዩ በጥናታቸው ያረጋገጡት ደግሞ የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ደጀኔ ኤርሚያስ ናቸው፡፡

አቶ ደጀኔ እንዳሉት ለወላድ እናቶች በጤና ተቋማት ውስጥ የማቆያ ማዕከላት አለመኖር ፣  በገጠሩ ማህበረሰብ አካባቢ የአምቡላንስ አገልግሎት በሚፈለገው ደረጃ ተደራሽ አለመሆንና ሌሎችም አገልግሎቶች የተሟሉ አለመሆናቸው በእናቶች ስነ ልቦና ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው።

በጤና ተቋማት የሚስተዋሉ የአገልግሎት ጥራት ችግሮችን ለማስወገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አቶ ደጀኔ አስገንዝበዋል፡፡

የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተከተል ጥለሁንበበኩላቸው "ሆስፒታሉ በዩኒቨርሲቲው ስር መካተቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰጡትን የጤና አገልግሎት በምርምር በመደገፍ ችግሮችን ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል" ብለዋል፡፡

በየጊዜው ከምሁራን የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ ስለሚደረጉ የሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ሪፈራል ሆስፒታሉ በዞኑ የሰው ኃይልና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ያለባቸውን ስምንት ጤና ጣቢያዎችና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የባለሙያ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳምክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አቡበከር ከድር በበኩላቸው የተመረጡ የምርምር ውጤቶችን ወደ ፕሮጀክት በመቀየር የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይ በዩኒቨርሲቲው የሚካሄዱ ምርምሮች ሥራ ላይ ውለው የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ተቋሙ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ላይ የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ምሁራን 18 ጥናታዊ ጽሁፎች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም