በዓድዋ ሥራ ያልጀመሩ 31 ባለሃብቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

55

አክሱም መጋቢት 10/2011 በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የዓድዋ ከተማ የኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ወደ ሥራ ላልገቡ 31 ባለሃብቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ገለጸ።

ባለሃብቶቹ የመሠረተ ልማት ተቋማት ሳይሟላላቸው ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ  አግባብ አይደለም ብለዋል።

በጽህፈት ቤቱ የከተማው የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ገብረኪዳን ዓለምሰገድ ለባለሃብቶቹ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ፈቃድ ወስደው ባስገቡት የፕሮጀክት የተግባር መተግበሪያ/ፕሮፖዛል/ መሠረት ሥራ ባለመጀመራቸው መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በመሆኑም በሦስት ወራት ውስጥ ወደ ምርት ካልገቡ ፈቃዳቸውን እንደሚሰረዝም አስጠንቅቀዋል።

ባለሃብቶቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ መሠረተ ልማት ተቋማት እንደተሟሉላቸውም አስተባባሪው አመልክተዋል።

እንዲያውም ያለፉት ሁለት ዓመታት ግንባታቸውን አጠናቅቀው አሁን ማምረት የሚጀምሩበት ወቅት ሊሆን ይገባ ነበር  ሲሉም  ተናግረዋል።

ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ባለሃብቶች መካከል  በማምረቻ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት መካከል አቶ ተክላይ ገብረ ሕይወት አንዱ ናቸው።

እንደ እሳቸው ገለጻ ባቀረቡት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት መሠረት ወደ ሥራ ያልገቡት የመሠረተ ልማት ተቋማት ስላልተሟሉላቸው መሆኑን  ይናገራሉ።

በተለይ በቂ የውሃና ኤሌክትሪክ መሥመሮች ባለመዘርጋታቸው ሥራቸውን ለመጀመር እንዳላስቻሏቸው ተናግረዋል።

በጽህፈት ቤቱ የተሰጠው የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት ባለሀብት ፣ በሦስት ወራት ውስጥ ወደ ምርት ለመግባት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል።

አቶ ኃይለማርያም መኮንን የተባሉ ባለሀብት በበኩላቸው ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት በራሳቸው ወጪ ውሃና ኤሌክትሪክ ማስገባታቸውን ይናገራሉ። ''መንግሥት እኛን ማበረታታት እንጂ፤ ማስፈራራት የለበትም'' ሲሉም ማስጠንቀቂያው ተገቢ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

መንግሥት ቃል በገባው መሠረት የአካባቢውን ተፋሰስ ልማት ሥራ በማጠናቀቅ  የጎርፍ ስጋትን እንዲያስወግድላቸው ጠይቀዋል።

በዚህ በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ማምረት እንደሚጀምሩ የገለጹት አቶ ኃይለማርያም በጽህፈት ቤቱ የተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በቂ አለመሆኑን ይናገራሉ።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 363 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በማምረቻ፣ በግብርናና በሆቴል ዘርፎች ሥራ መጀመራቸውን የዞኑ አስተዳደር የከተማ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም