በማዕከላዊ ጎንደር ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶችን ለማስከፈት እንቅስቃሴ ተጀመረ

68

ጎንደር መጋቢት 9/2011 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አራት ወረዳዎች በነበረው የጸጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ 80 ትምህርት ቤቶችን ለማስከፈት እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በጭልጋ ወረዳ በአደዛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ የመማር ማስተማር ስራ  የማስጀመር ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ወቅት የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን እርካቤ እንደተናገሩት ባለፉት አራት ወራት የነበረው የጸጥታ ችግር አሁን ተረጋግቶ በአካባቢዎቹ ሰላም ሰፍኗል፡፡

በዚህም  ተዘግተው ከነበሩ 100 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 80ዎቹ በተያዘው ሳምንት ሙሉ በሙሉ እንዲከፈቱ ይደረጋል፡፡

እንዲሁም በጊዜያዊ መጠለያዎች የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ በመጀመራቸው ለትምህርት ቤቶቹ መከፈት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

መምሪያው ወደ ትምህርት ገበታቸው ለሚመለሱ ችግረኛ ተማሪዎች ከ29ሺ በላይ የመማሪያ ደብተሮችን ጨምሮ እርሳስና እስክርቢቶ እንዲሁም ጥቁር ሰሌዳዎችንና ጠመኔዎችን ወደ ትምህርት ቤቶቹ ማድረስ መጀመሩን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት በነበረው ግጭት ተቃጥለው ጉዳት የደረሰባቸው አራት ትምህርት ቤቶች ደግሞ በቀጣዩ ዓመት ዳግም ተገንብተው ስራ እስኪጀምሩ  የትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎች ወደ አጎራባች ትምህርት ቤቶች ተዛውረው እንዲማሩ ይደረጋል፡፡

የቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቹም  ቅደመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ትምህርታቸውን ለማስጀመር ጥረት ይደረጋል ተብሏል፡፡

የጭልጋ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አቡሃይ ጌትነት በበኩላቸው በወረዳው በችግሩ ሳቢያ ተዘግተው የነበሩ 32 ትምህርት ቤቶች በተያዘው  ሳምንት ተከፍተው የማስተማር ስራ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ሰላም በመስፈኑ   ወላጆች ፣መምህራንና ተማሪዎችን በማወያየት ትምህርት ቤቶቹ እንዲከፈቱ ውሳኔ ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡

" በግጭቱ ትምህርት ቤታችን በመዘጋቱ በአይምባ ጊዜያዊ መጠለያ ከቤተሰቤ ጋር ለማሳለፍ ተገድጄ ነበር"  ያለው ደግሞ በጭልጋ ወረዳ የአደዛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ  አለም ወረደ ነው፡፡

ትምህርት ቤቱ በመከፈቱ መደሰቱንና የባከነባቸውን የትምህርት ጊዜ  ሌት ተቀን በማጥነት አካክሶ ለስምንተኛ  ክፍል ፈተና መዘጋጀቱንም ተናግሯል፡፡

የዚሁ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሱሌማን ሽፈራው በበኩሉ "ትምህርት በመቋረጡ ላለፉት ሶስት ወራት አልባሌ ቦታ ለመዋል ተገድጄ ነበር፤ ትምህርት ቤቴ በመከፈቱ እጅግ ተደስቻለሁ" ብሏል፡፡

በትምህርት ቤቱ የአራተኛ ክፍል የቋንቋ መምህርት የዝና ጫቅሌ በበኩሏ የባከነውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ በማካካስ ተማሪዎችን ለማብቃት መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ጭልጋ፣ ላይ አርማጭሆ፣ ምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ ወረዳዎች ውስጥ 100 ትምህርት ቤቶች ላለፉት አራት ወራት ተዘግተው ቆይተዋል፡፡

50ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ተለይተው መቆየታቸውንም ከዞኑ ትምህርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም