በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ሊኖር ስለሚገባው ሕጋዊ የሰዎች ዝውውር ላይ ያተኮረ ምክክር እየተካሄደ ነው

65

መቀሌ መጋቢት 9/2011 በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ሊኖር ስለሚገባው ሕጋዊ የሰዎች ዝውውር ጉዳይ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ዛሬ በመቀሌ ተጀምሯል።

በመድረኩ ከኢትዮጵያ የትግራይና የአማራ ክልሎችና ከሱዳን ደግሞ የገዳሪፍ ግዛት አመራሮች ተሳትፈዋል።

የትግራይ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኪሮስ ሐጎስ በዚሁ ወቅት በአገሮቹ መካካል በተናጠል የሚደረገው የጉልበት ሰራተኞች ዝውውር ለጉልበት ብዝብዛና እንግልት እየዳረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ዝውውሩ አገሮቹ ያደረጉትን ስምምነት መሠረት በማድረግ  ቢከናወን ለዜጎቹ  ደህንነት ከሚኖረው ጠቀሜታ ባለፈ፤ ለአገሮቹ መልካም ግንኙነት መጠናከር አስተዋፅኦ እንዳለው አስታውቀዋል።

የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አብደልቃድር ከድር ዩኒቨርሲያቸውና የገዳሪፍ ዩኒቨርሲቲ በሰዎች ዝውውር ዙሪያ በጋራ የጀመሩት እንቅስቃሴ  ወደ ሌሎች የምርምር ዘርፎች ለማስፋት እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

የገዳሪፍ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ኢብራሂም ዓብዱሰላም በበኩላቸው በአገሮቹ መካከል ያለው ዝውውር ለጋራ እድገትና ዘላቂ ጥቅም  ፋይዳ በሚሰጥ መልክ መያዝ ያስፈልገዋል ብለዋል።

የገዳሪፍ  ግዛት የአሰሪና ሠራተኛ ሚኒስቴር ተወካይ ሚስተር ናስር መሓመድ ዩሱፍ በአፍሪካ ቀንድ ካሉት አገሮች መካከል ከፍተኛ የሰዎች ዝውውር ከሚታይባቸው አገሮች መካከል ቀዳሚ  የሆኑት ሁለቱ አገሮች ሕጋዊ የሰዎች ዝውውርን ስትራቴጂያዊ  ዕቅድ መምራት እንደሚያሻቸው ጠቁመዋል።

በዚህም ለጋራ እድገታቸውና ተጠቃሚነታቸው የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ማሳደግ ይቻላልም ይላሉ።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ የአገሮቹ ተጎራባች ክልሎች የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በመቀሌና በገዳሪፍ ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር የተዘጋጀው መድረክ  እየተካሄደ ያለው ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

በአገሮቹ ወቅትን ጠብቀው በሚካሄዱ ሥራዎች ሳቢያ በየዓመቱ እስከ 400 ሺህ ሰዎች እንደሚንቀሳቀሱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም