እነ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው የተመሰረተባቸውን ክስ እንዳልፈፀሙ ተናገሩ

81

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2011 እነ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ መስጠትን አስመልክቶ የተመሰረተባቸውን ክስ እንዳልፈፀሙ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተናገሩ።

የፌዴራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ (ሜቴክ) የስራ ኃላፊዎች ላይ”የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ባላስተማራቸውና ባልተቀረጸ ሥርዓተ ትምህርት ሐሰተኛ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ እንዲሰጥ አድርገዋል” በማለት ስምንት ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

የተመሰረተው ክስ እንደሚያስረዳው ተምረውበታል የሚባለው የትምህርት ተቋም በማንም ዘንድ የማይታወቅ ሲሆን በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ ለማስተማር ዶክተር መኮንን ገብረሚካኤል በተባለ ተጠርጣሪና በቁጥጥር ስር ካልዋለ አንድ ግለሰብ ጋር እንደተከፈተ ያስረዳል።

ተጠርጣሪው ዶክተር መኮንን ገብረሚካኤል ራሳቸውን የትምህርት ተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አድርገው በማቅረብ፣  ከቀድሞ የሜቴክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር በሐሰተኛ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስም ከሜቴክ ጋር ለማስተማር የውል ስምምነት መፈራረሙንና የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘውም ማጽደቃቸውን ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ አመልክቷል።

ከሜጀር ጄነራል ክንፈ በተጨማሪም ብርጋዴር ጄነራል ጥጋቡ ፈትለ፣ ሻለቃ ገብረሥላሴ ገብረጊዮርጊስ፣ ሻለቃ ፋሲል አበራ፣ መቶ አለቃ ቶማስ ደረሰ፣ ወሰንየለህ ኃይለሚካኤል እና ሀድአት ወልደትንሳይ ከሐሰተኛ ትምህርት ተቋሙ ጋር በተያያዘ የውል ስምምነት መፈራረማቸውም ተጠቁሟል።

በመሆኑም ሁሉም ተከሳሾች ዛሬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በተካሔደው የእምነት ክሕደት ቃል አሰጣጥ ስነስርአት ላይ ወንጀሉን እንዳልፈፀሙ ነው የገለጹት።

ክሱን የመሰረተው ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ''ተከሳሾቹ ዛሬ በቀረበባቸው ክስ ላይ ክደው የተከራከሩ በመሆኑ ያሉኝ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች እንዲታይልኝ'' ሲል ነው ጥያቄ ያቀረበው።

በዚሁ መሰረትም ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን የምስክርነት ቃል ለማድመጥ ለግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም