በምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ ቲቤ ወረዳ በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ቡና ተያዘ

100

አምቦ  መጋቢት 9/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ ቲቤ ወረዳ በሕገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 400 ሺህ ብር ግምት ያለው ቡና መያዙን የወረዳው ፖሊስ ገለጸ።

ቡናው ባኮ ኬላ ላይ ትናንት የተያዘው የሠሌዳ  ቁጥር ኮድ 3 –53101 ኢትዮጵያ በሆነ  የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ ተጭኖ ከጊምቢ ወደ አዲስ አበባ ሲጓጓዘ መሆኑን የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ሳጂን አየለ ሞቱማ  አስታውቀዋል።

ባኮ ኬላ ላይ የተያዘው በትናንሽ ሻንጣዎችና ፌስታሎች ተቋጥሮ ለማሳለፍ ሲሞከር የተያዘው ቡና መጠኑ 4ሺህ 565 ኪሎ ግራም ነው ብለዋል።

አሽከርካሪው ለጊዜው ቢሰወርም፤ ቡናውን በኤግዚቢትነት ተይዞ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ ሕገወጥ እንቅስቃሴን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ኅብረተሰቡ አጥፊዎችን በመጠቆም እንዲተባበርም አዛዡ ጠይቀዋል።

የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አንዳንድ ኬላዎች በቅርቡ በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችና የቡና እንቅስቃሴ ማዕከል ሆኖ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም