በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ሆስፒታል ተመረቀ

61

ነቀምት መጋቢት 9/2011 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ ወረዳ ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የአቤ ደንጎሮ ሆስፒታል ትናንት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ሆስፒታሉ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱ  እንዳስደሰታቸው አንዳንድ የወረዳው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጃ ዱጉማ በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው  ሆስፒታል የተመላላሽ፣ የአስተኝቶ ማከም፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የቀዶ ሕክምና፣ የድንገተኛ ሕክምና፣ የራጅ፣ የላቦራቶሪና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አሉት።

ሆስፒታሉ በአቤ ደንጎሮ ወረዳና በአካባቢው በሚገኙ ተጎራባች ወረዳዎች ለሚገኙ ከ400 ሺህ ለሚበልጡ ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ የሕክምና መሳሪያዎችና የሰው ኃይል የተሟላለት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው ሆስፒታሉ የህዝቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ የመለሰና የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ሆስፒታሉ የራሱ ሀብትና ንብረት መሆኑን ተረድቶ እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቀው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በበኩላቸው ሆስፒታሉ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል የቱሉ ዋዩ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እቴነሽ ደገፉ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው ለበርካታ ዓመታት የጤና ተቋማት ባለመኖሩ በተለይ በእናቶችና ህጻናት ህይወት ላይ አደጋ ይደርስ እንደነበር አስታውሰዋል።

የወረዳው ህዝብ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ሻምቡና ነቀምቴ ሆስፒታሎች በመጓዝ ለወጪና እንግሊት ሲጋለጥ መቆየቱንም ጠቁመዋል።

በአካባቢያችን ደረጃውን የተጠበቀ ሆስፒታል መገንባቱ ወጪና እንግልትን ከማስቀረቱም በላይ የእናቶችና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ  አቶ ደቻሣ ገለታ ወረዳው ከነቀምቴና ሻምቡ ሆስፒታሎች በብዙ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ስለሚገኝ በተለይ በወሊድ ጊዜ የበርካታ እናቶችና ህፃናት ህይወት ሲያልፍ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

የሆስፒታል መገንባት የአካባቢውን ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ  የመለሰና የህብረተሰቡን የጤና ችግር የሚፈታ በመሆኑ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ መጋቢት 07 ቀን 2011 በዞኑ በጉዱሩ ወረዳ በ56 ሚሊዮን የተገነባ ሆስፒታል ተመርቆ አገልግሎት መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም