የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ተካሄዱ

91

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ተካሄዱ።

ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተካሄደ ጨዋታ ፌዴራል ፖሊስ መከላከያን 30 ለ 26 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ድሬዳዋ ላይ ቡታጅራ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 17 ለ 16 ማሸነፍ ችሏል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መቐለ ሰብዓ እንደርታን 25 ለ 22 በማሸነፍ መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል አስመዝግቧል።

በአዲስ አበባ በተደረገ ሌላ ጨዋታ የአምናው የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጎንደር ከተማን 34 ለ 26 በማሸነፍ የሊጉን መሪ እግር በእግር እየተከተለ ይገኛል።

በዘጠነኛው ሳምንት መርሃ-ግብር ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና ከምባታ ዱራሜ ጨዋታ አላደረጉም።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ16 ነጥብ ሲመራ፤ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ15 ነጥብ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ11 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

እስካሁን በፕሪሚየር ሊጉ ምንም ጨዋታ ያላሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ያለ ምንም ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

በተያያዘ ነገ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከጎንደር ከተማ የሊጉ ተስተካካይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሁለቱ ክለቦች በዘጠነኛ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ጨዋታቸውን ያደረጉ ሲሆን ጎንደር ከተማ ባለበት የፋይናንስ ችግር ተስተካካይ ጨዋታውን መቐለ ማድረግ እንደማይችልና ጨዋታው አዲስ አበባ እንዲደረግ ለመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከስምምነት ላይ በመድረሱ ነገ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የሚያደርጉ ይሆናል። 

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር በያዝነው ሳምንት መጨረሻ ቀናት በሚካሄዱ ተስተካካይ ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የምድብ አንድና ሁለት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሄደዋል።

ትናንት ባህርዳር ወልቂጤ ከተማ ቢጂአይ ኢትዮጵያን 60 ለ 33 ከትናንት በስቲያ ባህርዳር ላይ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን አማካሪ ወልቂጤ ከተማን 44 ለ 40 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

አርብ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ባህርዳር ላይ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ቢጂአይ ኢትዮጵያን 64 ለ 30 በሆነ ውጤት ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በምድብ ሁለት ትናንት ሀዋሳ ላይ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጎንደር ከተማን 49 ለ 44 ሀዋሳ ላይ ከትናንት በስቲያ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሀዋሳ ከተማን 46 ለ 35 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

አርብ መጋቢት 6 ቀን 2011 ዓ.ም  ሀዋሳ ላይ ጎንደር ከተማ ሀዋሳ ከተማን 49 ለ 40 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የውድድር ፎርማት መሰረት በሴቶች በምድብ አንድና ሁለት ያሉ ክለቦች በቅደም ተከተል ወደ ባህርዳርና ሀዋሳ በማቅናት ለሶስት ተከታታይ ቀናት እርስ በርስ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በሁለቱም ጾታዎች በተመሳሳይ ስድስት ክለቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም