የአባያን ሐይቅ ከእንቦጭ አረም ለመታደግ አየተካሄደ ባለው ዘመቻ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ አነስተኛ ነው—-ነዋሪዎች

492

    አርባ ምንጭ መጋቢት 9/2011 የአባያን ሐይቅ ከእምቦጭ አረም ለመታደግ እየተካሄደ ባለው የዘመቻ ሥራ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን ነዋሪዎች ገለፁ።

ከሦስት ሳምንት ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የአረም ማስወገድ ሥራ እንደቀጠለ ነው።

በአረም ማስወገዱ እየተሳተፉ ካሉ ነዋሪዎች መካከል የጋሞ ዞን ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ባልደረባ ወይዘሮ ፍቅርተ ዘርሁን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በሐይቁ አካባቢ የተከሰተው አረም አስደንጋጭ ነው።

“የአረሙ ስርጭት ቶሎ ካልተገታ ሐይቁን ከመጥፋት ማዳን አይቻልም” ያሉት ወይዘሮ ፍቅርተ አረሙን በማስወገድ በኩል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከጠበቁት በታች መሆኑ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።

“በአረም ማስወገድ ዘመቻው የህዝብ ተሳትፎ አነስተኛ ሆኖ ሳይ ቅር ብሎኛል” ያሉት ደግሞ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚኖሩት አቶ ሙልጌታ ግርማ ናቸው።

“መጀመሪያ በሐይቁ ውስጥ ያሉ እንስሳት በሰው ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ስጋት ነበረኝ፤  ይሁንና አረም የመከላከሉ ሥራ ከሐይቁ ውጭ በመሆኑ ያለስጋት እየተሳተፍኩ ነው” ብለዋል።

በጎ ፍቃደኛ ጃፓናዊ ወጣት ኩኒ አኪ በበኩሉ ከአረሙ ስርጭት አኳያ በመከላከሉ ሥራው እየተሳተፈ ያለው ህዝብ ቁጥር አነስተኛ መሆኑን እንደተገነዘበ ገለጿል ።

“በአረም ማስወገዱ ሥራ ብዛት ያለው ሰው ከተሳተፈ አረሙን በነቀላ ብቻ ማስወገድ ይቻላል” ያለው ወጣት ኩኒ አረሙ በስነ ምህዳር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ በመሆኑ የማስወገዱ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና እሱም በመሳተፉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።

የጋሞ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማዜ ሸቀኔ በበኩላቸው አረሙ በሐይቁ ዙሪያ በ2ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መከሰቱን አመልክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት ከየካቲት 2011 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ከአርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያ ወረዳ እንዲሁም ከምዕራብ አባያ ወረዳ የተውጣጡ 33ሺህ 356 የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የአረም ማስወገድ ዘመቻ እየተካሄደ ነው።

በዘመቻው እስካሁን በ58 ሄክታር ላይ የነበረው የእንቦጭ አረም የተወገደ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር አረም የማስወገድ ስራው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።