የዩኒቨርሲቲውን የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታልን ለማዘመን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል - ኢዜአ አማርኛ
የዩኒቨርሲቲውን የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታልን ለማዘመን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል
ሶዶ መጋቢት 9/2011 የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታልን ለማዘመን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ።
ሆስፒታሉ የሚስተዋሉበትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለማሻሻል በ100 ቀናት ዕቅዱ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታከለ ታደሰ እንደገለጹት ለሆስፒታሉ የተመደበው በጀት የሕክምና አገልግሎት አሰጣጡን የሚያሻሽሉ የግብዓቶች ግዢ፣ የሰው ኃይል ልማትና አደረጃጀቶችን ለማጠናከር ይውላል።
የሲቲ ስካን፣የኤም አር አይ፣የኩላሊት እጥበት ሕክምና የሚሰጡና መሰል ዘመናዊ መሣሪያዎች ግዢ እንደሚፈጸምበትም አስረድተዋል።
የሕክምና መንደር ግንባታው ለማካሄድ ጨረታ መውጣቱን ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ ካሉት ተገልጋዮች ብዛት አኳያ የሚመደብለት የሰው ኃይልና ገንዘብ በአግባቡ ባለመመራቱ አገልግሎቱን ሳይሻሽል ቆይቷል ብለዋል።
በየጊዜው የሚወጡ ዕቅዶች የተገልጋዮችን ፍላጎትና እርካታን መሠረት ያላደረጉና ተጠያቂነትን ባለማካተታቸው ተጨባጭ ለውጥ አለማምጣታቸውን ዶክተር ታከለ አመልክተዋል።
ችግሮቹ ለመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ሆነው መቆየታቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ዕቅዱ ተግባር ላይ ሲውል ችግሮቹ እንደሚፈቱ ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ የተጓተቱ መሠረተ ልማት ተቋማት ተፈጻሚ እንደሚሆኑም አመልክተዋል።
በሆስፒታሉ የድንገተኛ ሕክምና ክፍል ሐኪም አቶ ወንድሙ ወልዴ የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሠራተኛውን እርካታ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ለዕቅዱ ስኬታማት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
በሆስፒታሉ የፋይናንስ ሠራተኛ አቶ ዘለቀ ፋልታሞ በበኩላቸው ለዕቅዱ ውጤታማነት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፒታል ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።