በማቻከል ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ

70

ደብረማርቆስ መጋቢት 9/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ ትናንት በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በ14 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት አስተባበሪ ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ከደረሰኝ ወደ አማኑኤል ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-05430 አ.ማ የሆነ አይሱዙ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በመገልበጡ ነው።

ትላንት ከቀኑ 8:00 ሰዓት ላይ በደረሰው አደጋ ወዲያውኑ ሕይወታቸውን ያጡ የሁለት ሴቶች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው መሰጠቱን ተናግረዋል።

ሌሎች 14 ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በደብረማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙ ተደርጓል።

የአደጋው መንስኤ ከተፈቀደ ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር መሆኑን የገለጹት ኢንስፔክተሩ አሽከርካሪው ለጊዜው መሰወሩንና ፖሊስም ግለሰቡን ለመያዝ በክትትል ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም