ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት በሙሉ አቅሙ ይሰራል….ዶክተር አብይ አህመድ

884

ዲላ መጋቢት 8/2011 የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት በሙሉ አቅሙ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ከፌዴራልና ከክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን ተፈናቅለው በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ የተጠለሉ ዜጎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ጉብኝታቸውን ተከትሎ ከተፈናቃይ ተወካዮች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ዛሬ በመካከላችሁ የተገኝሁት ያላችሁበትን ሁኔታ ከሪፖርት ባለፈ በአካል በማየት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በማሰብ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የጌዴኦና ጉጂ ህዝቦች ከማንም በላይ ለዘመናት አብረው የኖሩ፣ በቋንቋና በባህል የተሳሰሩ ወድማማች ህዝቦች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

” ጥቂት ግለሰቦች በፈጠሩት ችግር ተፈናቃዮች አሁን ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ሁኔታውን ለመቀየር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ።

ተፈናቃዮች በበኩላቸው በተደጋጋሚ እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት በመፍራት ከምዕራብ ጉጂ ወደ ጌዴኦ ዞን ቢሰደዱም ለእለት ጉርስ የሚሆን ምንም አይነት ድጋፍ ባለማግኘታቸው ለረሃብና ለእንግልት መጋለጣቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ ተፈናቃዮች መካከል ወይዘሪት ትዕግስት ቦራ “ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘግይተው ቢመጡም በቀጣይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሮቻችን ይቃለላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብላለች

“ተፈናቅለን በችግር ውስጥ እያለን እርዳታ እየደረሰ ነው ተብሎ በሚዲያ የሚሰጠው መግለጫ ስህተት” ነው ያለችው ወይዘሪት ተዕግስት፣ በተለይ በረሃብ ውስጥ ለሚገኙ ህጻናትና አጥቢ እናቶች ሰብዓዊ ድጋፍ በፍጥነት እንዲደርስ ጠይቃለች።

“ተፈናቅለን ለዚህ መከራና ስቃይ የበቃነው የማንነት ጥያቄ በማንሳታችን ብቻ ነው” ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተፈናቃይና አስተያየት ሰጪ አቶ ተሰማ ኡዶ ናቸው።

ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልጸው መንግስት ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ ያደረገውን ጥሪ በመቀበል ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው እንደነበርም አስታውሰዋል።

” መንግስት በተለይ የህግ የበላይነትን በማስከበርና ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም ላይ በሚፈለገው ደረጃ ጠንክሮ ባለመስራቱ ለሌላ መፍናቀልና ሞት ተጋልጠና” በማለት ተናግረዋል።

ባለፉት ስምንት ወራት ወደቤታቸው ሳይመለሱ በመጠለያ ከማሳለፋቸው ጋር ተያይዞ መስራት ባለመቻላቸው ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት ተፈናቃዩቹ መንግስት በአስቸኳይ ስብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

የተፈናቃዮችን ቅሬታ ያዳመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበኩላቸው ባለፈው መፈናቅል ተፈናቀዮች ወደቄያችሁ ተመልሰው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ጥረት ቢደረግም በምእራብ ጉጂ ዞን በነበረ የጸጥታ ችግር ምክንያት እርዳታው በአግባቡ ተፈናቃዮች ጋር ሳይደርስ መቅረቱን አመልክተዋል።

በእዚህና መንግስት በሚፈለገው ልክ ማገዝ ባለመቻሉ ምክንያት ተፈናቃዮች ችግር ውስጥ መውደቃቸውን አስረድተዋል።

ያለውን ችግር ሙሉ በሙሉ በመፍታት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት በቀጣይ በሙሉ አቅሙ ይሰራል ሱሉም ተናግረዋል።

“የጉጂ ህዝብ የጌዴኦን ህዝብ ያፈናቅላል የሚል እምነት የለኝም” ያሉት ዶክተር አብይ፣ “ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ሰዎች በህግ እንዲቀጡ ይደረጋል፤ በዚህም ህግ ለሁሉም እኩል መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል” ብለዋል።

የተፈናቃይ ልየታ በማድረግ ከዛሬ ጀምሮ በሙሉ አቅም የምግብ ስርጭት እንደሚጀመር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሁለት ወንደማማች ህዝቦች መካከል መቃቃሩ ሰፍቶ ወደ አላስፈላግ ሁኔታ ወስጥ ሳይገባ አሁን ያለውን ስሜት በመቀነሰ ለሰላም እድል መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

“ተበድለንም ቢሆን በዳይን ይቅር በማለት ሌሎችን ማስተማር ይገባል” ሲሉም ዶክተር አብይ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።