ወላይታ ድቻና ስሁል ሽሬ አቻ ተለያዩ

78

ሶዶ  መጋቢት 8/2011 በወላይታ ሶዶ ስታዲየም ዛሬ የተገናኙት ወላይታ ድቻና ስሁል ሽሬ አቻ ተለያዩ።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት 2ኛ ዙር ጨዋታ መርሃ ግብር መሠረት ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተለይ አስከ 15ኛው ደቂቃ ድረስ ባለሜዳው ወላይታ ድቻ ተጭኖ በመጫወት ጥሩ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችሏል፡፡

በእዚህም በ10ኛው ደቂቃ ላይ 10 ቁጥር ለባሹ ባዬ ገዛኸኝ ከመሀል ሜዳ በቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ የራሱን ብቃት በማከል ወደጎል መቀየር ችሏል፡፡

ግቡን ተከትሎ ስሑል ሽሬ  የመሀል ሜዳን ከመቆጣጠርና የግብ ሙከራዎችን ከማድረግ አንጻር የመጀመሪያው አጋማሽ አስኪጠናቀቅ ድረስ የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል፡፡

ከዕረፍት መልስ ስሑል ሽሬ በመከላከል፣ ኳስ በማደራጀት፣ በማጥቃትና ቶሎ ቶሎ ወደተጋጣሚው የግብ ክልል በመድረስ የተሻለ ነበር፡፡

በዚህ ሂደት የድቻ ተከላካዮችና የግብ ጠባቂውን ስህተትና ያለመናበብ ችግር ተጠቅሞ በ51ኛው ደቂቃ ላይ 22 ቁጥር የለበሰው የስሁል ሽሬው ደሳለኝ ደባሽ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል፡፡

በአጠቃላይ የጨዋታ እንቅስቃሴና ሳቢ የኳስ ጨዋታ በማሳየት እንግዳው ስሑል ሽሬ የተሻለ ነበር፡፡

የወላይታ ድቻ ምክትል አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ተጨዋቾቹ ያሳዩት እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ቢሆንም የተገኘውን ነጥብ ማስጠበቅ ባለመቻላቸውና ባስመዘገቡት ውጤቱ መከፋታቸውን ተናግረዋል፡፡

ክለቡን ለማጠናከር የተጨዋቾች ዝውውርና መሰል ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው "በቀጣይ ውድድር ስህተታችንን አርመን ወደማሸነፍ እንመለሳለን" ብለዋል፡፡

"ተጋጣሚያችን የተከተለው ረጃጅም የኳስ አጨዋወትን ዝንባሌ በማጥናት ባደረግነው የጨዋታ ለውጥ በተለይም በመሀል ሜዳ ክፍል ብልጫ መውሰዳችን ነጥብ እንድንጋራ" እድርጎናል" ያሉት ደግሞ የስሑል ሽሬ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ናቸው፡፡

ለተጋጣሚው ቡድን ያላቸውን ክብር ገልጸው ከወራጅ ቀጠና ለመወጣት ጠንክረው እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት፡፡

ጨዋታውን በኮሚሽነርነት መላኩ በቀለና በዋና ዳኝነት ፌዴራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ መርተውታል፡፡

በጨዋታው መጀመሪያ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ እየበረረ በተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ህይወታቸውን ላጡ ለተለያዩ ሀገራት ዜጎች የህሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡

ከዚህ ባለፈም የወላይታ ደቻ ደጋፊዎች በአካባቢው ወጣቶች አነሳሽነት በደቡብ ክልል ገዴኦ ዞን በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ ላሉ ዜጎች ከ50 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ሰብስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም