በኩታገጠም ማሳ ያለማነውን የጓሮ አትክልት በጅምላ በመሸጥ ተጠቃሚ ሆነናል---- አርሶ አደሮች

60

ሽሬ እንዳስላሴ  መጋቢት 8/2011 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን በበጋ ወቅት በመስኖ ታግዘው በኩታ ገጠም ማሳ የጓሮ አትክልት ያለሙ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በጅምላ በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ።

የኩታ ገጠም ልማቱ የተሻለ የምርት መጠን እንዲያገኙ እንደረዳቸውም አርሶ አደሮቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል ።

በዞኑ መደባይ ዛና ወረዳ “ባሕራ”  ቀበሌ ገበሬ ማህበር  ወራጅ ወንዝ በመጥለፍ በኩታገጠም ማሳ ላይ የጓሮ አትክልት ካለሙ መካከል አርሶ አደር ሙዑዝ ጸጋይ ይገኙበታል፡፡

አርሶ አደሩ እንደሉት ዘንድሮ የመሬት ይዞታቸው የሚገናኝ አርሶ አደሮች በመስኖ ታግዘው በኩታ ገጠም ማሳ ላይ የጓሮ አትክልት በመስመር ዘርተዋል።

"በኩታ ገጠም  ማሳ ላይ ማልማት በመጀመራቸው ተገቢውን የባለሙያ ድጋፍና ክትትል በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

"በተመሳሳይ ጊዜ አንድ አይነት የጓሮ አትክልት ማልማታችን ደግሞ ተክሉን በቀላሉ ለመንከባከብና ተባይ ለመከላከል በማገዙ ከዘልማዱ አሰራር የተሻ የምርት መጠን እንድናገኝ አስችሎናል" ብለዋል ።

አርሶ አደር ሙዑዝ እንዳሉት ከአንድ ሄክታር ኩታገጠም ማሳቸው ላይ ያገኙት 84 ኩንታል ቀይ ሽንኩርት ከዚህ ቀደም ከሚያገኙት በእጥፍ ብልጫ አለው።

"በኩታ ገጠም ማሳ ላይ ያለማነው ሽንኩርት በአንድ ጊዜ በመድረሱ ምርቱን አንድ ላይ ሰብስበን ሳይባክን በጅምላ በመሸጣችን የተሻለ ተጠቃሚ አድርጎናል" ብለዋል ።

ከተሸጠው ምርት በግላቸው ከ90 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

“ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን በኩታ ገጠም ማልማት በመቻሌ ያገኘሁትን ምርት ሳይባክን በትኩሱ ለገበያ ማቅረብ ችያለሁ " ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ህሉፍ አባይ ናቸው ።

"አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ማሳ ላይ ያለማነውን ቲማቲም አንድ ላይ ሰብሰበን በጅምላ ለገበያ በማቅረባችን ተጠቃሚ ሆነናል" ብለዋል።

"እንደ አርሶ አደር ህሉፍ ገለጻ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ሆነው በአንድ ጊዜ ብዙ ምርት ማቅረባቸው ምርታቸውን ለነጋዴዎች በፍጥነትና በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ አስችሏቸዋል።

"ነጋዴዎች ገጠር ቀበሌ ደረስ መኪና ይዘው በመዝለቅ ምርታችንን እየገዙን ነው" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በተናጠልና በዘልማድ ከአንድ ሄክታር ማሳ ከሚያለሙት ሽንኩርት 15 ኩንታል ያገኙ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደር ህሉፍ ዘንድሮ ከተመሳሳይ ኩታገጠም ማሳ 90 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በቡድን ከተሸጠው ምርት በግላቸው 100 ሺህ ብር ገቢ ማገኘታቸውን ተናግረዋል ።

በዞኑ በታህታይ ቆራሮ ወረዳ “ሰመማ” ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ግርማይ ተክለሃይማኖት በበኩላቸው በመስኖ በመታገዝ በኩታ ገጠም ማሳ ማልማት ከጀመሩ ሦስት ዓመታት እንደሞላቸው ተናግረዋል ።

"በዓመታቱ ውስጥ የማገኘው ምርት በብዛትም ሆነ በጥራት እየጨመረ ነው" ብለዋል ።

አርሶ አደር ግርማይ እንዳሉት በዘንድሮው የበጋ ወቅት በመጀመርያው ዙር  በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ ካለሙት ሰላጣና ቆስጣ ሽያጭ ከ80 ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል ።

"ምርቴን ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ሰብስቤ ለሽያጭ ስለማቅርብ የምርት ብልሽትና ብክነት አይገጥመኝም" ሲሉም ገልጸዋል።

የዞኑ የመስኖ ልማት አስተባባሪ አቶ ሚኪኤለ ተስፋይ በበኩላቸው በበጋው ወቅት በመጀመርያው ዙር ከ2 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ ኩታገጠም ማሳ ላይ የጓሮ አትክልት ልማት መካሄዱን ተናግረዋል ።

"ከለማው ማሳ 200 ሺህ ኩንታል  ምርት ተሰብሰቧል" ያሉት አስተባባሪው በልማቱም ከ3 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም