የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተከሌ 'ቪላ አልፋ' እድሳት ከ2 ወራት በኋላ ይጠናቀቃል

212

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2011 እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የስነ ጥበብ ስራ ቦታና መኖሪያ የነበረው 'ቪላ አልፋ' ዕድሳት ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ።

ዕድሳቱን በማጠናቀቅ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በጥበብ ቤተ መዘክርነት ለጎብኝዎች ክፍት እንደሚደረግም ተገልጿሏል።

በ2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታዋቂው ሰዓሊ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወረቅ ተክሌ ጦር ኃይሎች አካባቢ የሚገኘውን 'ቪላ አልፋ' የተሰኘውን የመኖሪያና የስዕል ጋለሪ ግቢ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ እንዲተላለፍ ከሕልፈታቸው በፊት ተናዘው ነበር።

በ1961ዓ.ም የተገነባው ቪላ አልፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕንጻ ጥበብ ኮሌጅ አማካሪነትና የሻርፕ ኢንጂነሪንግ ኤንደ ሲስተም ሶሉሽን በተባለ ተቋራጭ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ባለቤትነት ከ3 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ ዕድሳቱ እየተካሄደ ነው።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒሰትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ከቅርስ ጥበቃ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ዛሬ የዕድሳቱን ሂደቱን ጎብኝተዋል።

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዘክር ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ አርቲስቱ ካለፉ  በኋላ በቤተሰባቸው "ይገባኛል" ጥያቄ ለብዙ ጊዜ በህግ ጉዳይ ተይዞ የነበረውን 'ቪላ አልፋ'  በፍጥነት አድሶ ለጎብኝዎች ክፍት ማድረግ አለመቻሉን አስታውሰዋል።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ጥበቃ ሲደረግለት የቆየው 'ቪላ አልፋ' የፍርድ ሂደቱ ከተጠናቃቀ በኋላ፤ የባለሙያዎች ኮሚቴ ተዋቅሮ ተገቢው የስዕልና ግል ንብረት ቆጠራና ምዝገባ ስራዎች ተከናውነው ከለፈው ዓመት ጀምሮ እድሳት ላይ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት።

'ቪላ አልፋ' ሲታደስም የሰዓሊው የጥበብ ስራዎች ቀድሞ በተደራጁበት መልኩ ካለምንም መዛነፍ እንዲቀመጡ ለማድረግ የቆጠራና የምዝገባ ስራው ረጂም ጊዜ መውሰዱን ገልጸዋል።

ከምዝገባና ቆጠራ በኋላም እድሳቱ እሰኪጠናቀቅ በቪላው ውስጥ የተገኙ ከ400 በላይ የሚሆኑ ስዕላት፣ የመገልገያ ቁሳቁሶችና ንብረቶች ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ በጊዜያዊ ክፍል እንዲቀመጡ መደረጉን ነው ያብራሩት።

ዕድሳቱን የሚያከናውነው የሻርፕ ኢንጂነሪንግ ኤንደ ሲስተም ሶሉሽን ተቋራጭ ተወካይ አቶ ሸምሰዲን ዳውድ እንዳሉት ስዕላቱም ሆነ ሌሎች ንብረቶች ሳይጎዱ በጥንቃቄ ማቆያ ክፍሎች ተሰርተውለት እየተጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

የቤቱ ጣሪያና ኮርኔስ   በማፍሰሳቸው የውስጥ ግድግዳዎች ተጎድተው እንደነበር ገልጾ፣ ከጣሪያ እስከ ግድግዳ ያሉ ስራዎችን የሰዓሊውን ቀደምት የአሰራር ጥበብ ተከትለው የታደሱ ናቸው ብለዋል።

ቀለም ቀቢዎችም የስዕልን ጥበብ የሚያውቁ ሰዓሊዎች መሆናቸውን ነው ያስረዱት።

ከተወሰኑ ክፍሎች በስተቀር የቪላው ውስጣዊ ክፍሎች አጠቃላይ ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸው፤ ተቋራጩ የውጭ ግድግዳዎችንና ሌሎች የዕድሳት ስራዎችን ከሁለት እስከ ሶሰት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ሰርቶ እንደሚያስረክብ አረጋግጠዋል።

የዕድሳት ሂደቱን የተመለኩት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንዳሉት በልዩ የቤት አሰራር ጥበብ የተገነባውና በስዕላት ጥበብ ያሸበረቀው የሰዓሊው መኖሪያ ግቢ፤ የአርቲስቱን የጥበብ ፍልስፍና የሚዘክር ግቢ ነው።

"ቪላ አልፋ ለኢትዮጵያዊያን ብዙ ትምህርት ያስተምራል" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሙያን ማክበር፤ ራስን የመምራትና በስርዓት የመኖርን ምስጢር የሚያስተምር ተቋም ይሆናል ብለዋል።

ግቢው የሙያ ብቻ ሳይሆን ለልጆች ትልቅ የሰብዕና መገንቢያ ተቋም እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸው፤ እድሳቱ በፍጥነት ተጠናቆ በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ለጎብኝዎች ክፍት እንደሚሆን ተናገረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም