ላሊበላን ለዓለም ህዝብ የሚያስተዋውቀው የ'አረንጓዴ መብራት ፕሮጀክት' ይፋ ሆነ

96

አዲስ አበባ  መጋቢት 8/2011 የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያንን በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለዓለም ህዝብ የሚያስተዋውቅ የ'አረንጓዴ መብራት ፕሮጀክት' ትናንት ምሽት በአየርላንድ መንግስት ይፋ ተደረገ።

ኢትዮጵያና አየርላንድ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል በዚህ በተያዘው መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም እየተከበረ ነው።

ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል ቤተ ጊዮርጊስን በምሽት በአረንጓዴ መብራት ያለውን መስህብ ለዓለም ህዝብ ለማስተዋወቅ የፊልም ቀረጻ ሥነ ስርዓት በኢትዮጵያ የአየርላንድ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ሚስተር ፓትሪክ ማክማነስ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ ሚስተር ፓትሪክ ማሽ ማርስ እንዳሉት፤ የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኦ ቫራድካር በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል የባህል ልውውጥ ለማድረግ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በተለይም በባህላዊና በታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ላይ በትብብር ለመስራት አየርላንድ ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኦ ቫራድካር ማረጋገጣቸውን ተወካዩ ገልጸዋል።

በአየርላንድ መንግስት የሚደገፈው ዓለም አቀፉ የ'አረንጓዴ መብራት ፕሮጀክት' በኢትዮጵያ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል ቤተ ጊዮርጊስን በምሽት በአረንጓዴ መብራት በመቅረጽ ያለውን መስህብ ለዓለም ህዝብ ማስተዋወቅ ነው።

ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት የአክሱም ሐውልትን፣ ብሔራዊ ትያትር ቤት አጠገብ የሚገኘውን የአንበሳ ሐውልትና የኢትዮጵያ የአየር መንገድን በምሽት በአረንጓዴ መብራት በመቅረጽ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለዓለም ህዝብ እንዲተዋወቅ አድርጓል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ገብርኤል አስፋው በበኩላቸው ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ፕሮጀክት ቤተ ጊዮርጊስን ለመላው ዓለም በማስተዋወቅ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።

የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ላይ ለሚያደርገው ድጋፍም አቶ ገብርኤል ምስጋና አቅርበዋል።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ማዕከል /ዩኔስኮ/ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግብዣ የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኦ ቫራድካር ከጥር 1 እስከ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። 

በኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን ጥበቃና እንክብካቤን ለማጠናከር አየርላንድ ያላትን ልምድና ዕውቀት ለማካፈል በትብብር እንደምትሰራም በጉብኝታቸው ወቅት ተናግረው ነበር። 

በተለይም ላሊበላን የዓለም አቀፍ ጎብኚዎች መዳረሻ በማድረግ ቅርሶችን ለምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት፣ ለገጠር ቱሪዝምና ለስራ ዕድል ፈጠራ ለማዋል የአየርላንድ መንግስት በትብብር እንደሚሰራ ማረጋገጣቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያና አየርላንድ 25 ዓመታትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን አየርላንድ ኤምባሲዋን በ1986 ዓ.ም አዲስ አበባ  ከፍታለች።

ኢትዮጵያም ኤምባሲዋን ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በደብሊን ከተማ በመክፈት ሁለቱ አገሮች በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤናና በምግብ ዋስትና መርሐ ግብር በትብብር በመስራት ላይ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም