በተደረገላቸው ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን በጋምቤላ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች ተናገሩ

63

ጋምቤላ መጋቢት 8/2011 በጋምቤላ ከተማ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ግለሰቦች በማህብረሰብ አገልግሎት፣ ጤናና ልማት ድርጅት በተደረገላቸው ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

ከክልሉ እገዛ የሚፈልጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እያከናወኑት ያለውን ሥራ ሊያጠናክሩ እንደሚገባም የክልሉ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

በከተማዋ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው ግለሰቦች ለኢዜአ እንዳሉት ድርጅቱ ነጻ የሕክምና አገልግሎትን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሥልጠና እየሰጣቸው ነው ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በማህበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ የገንዘብ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ አዲሱ ተካ ከዚህ በፊት በጉልበት ሥራ ተሰማርተው ሕይወታቸውን ሲመሩ እንደነበር አስታውሰው በእዚህም በሽታውን ለመከላከል የሚወስዱትን መድኃኒት ለመቋቋም ከብዷቸው እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችል ሥልጠና በድርጅቱ በኩል እየተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰው በእዚህም በቀጣይ ችግራቸው ይፈታል የሚል እመነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

" ከዚህ በፊት በገንዘብ አጥረት እንቸገር ነበር፤ ይህ ድርጅት ድጋፍ ማድረግ ከጀመረ በኋላ ከራሳችን አልፎ ቤተሰባችን ጭምር ነጻ የሕክምና አገልግሎት እያገኘ ነው " ያሉት ደግሞ አቶ ኡኩቡ ኪር ናቸው፡፡

አቶ ኡኩቡ እንዳሉት ድርጅቱ ከጤና ድጋፍ በተጨማሪ በማህበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለእያንዳንዳቸው ሥልጠናና የሦስት ሺህ ብር ድጋፍ አድርጎላቸዋል፡፡

የድርጅቱ ድጋፍ በቀጣይ የተሻለ ሕይወት ለመምራት እንደሚያግዛቸው የተናገሩት አቶ ኡኩቡ በቀጣይም መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከጎናቸው በመሆኑ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡

"ድርጅቱ ለመድኃኒት መግዣ በሰጠኝ የገንዘብ ድጋፍ መድኃኒት ተጠቃሚ መሆን ጀምሪያለሁ" ያሉት ደግሞ ሌላው ተጠቃሚ አቶ መሐመድ ሁሴን ናቸው።

መድኃኒት መጠቀም ከጀመሩ በኋላ ጤናቸው በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱንም ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ገዳሙ እንዳሉት በክልሉ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል።

ድርጅቶቹ በተለይ በክልሉ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸውን ወገኖችን ለመደገፍ የሚደርጉትን ጥረት በማገዝ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የማህበራዊ አገልግሎት፣ የጤናና ልማት ድርጅት ጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እያደረገ ያለው ድጋፍ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች ሕይወት እንዲሻሻል ማድረጉን ጠቁመው መንግስት ለድርጅቱ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡

የማህበራዊ አገልግሎት፣ የጤናና ልማት ድርጅት ጋምቤላ ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ ተፈራ ታደሰ ድርጅቱ አሁን አገልግሎት ከሚሰጥባቸው የጋምቤላ ከተማ፣ ኢታንግ ልዩ ወረዳና ጎግ በተጨማሪ በጎደሬና በአቦቦ ወረዳዎች ላይ አገልግሎቱን ለማስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ 15 ሺህ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንና በቀጣይም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትን ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም በህብረት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

አቶ ተፈራ እንዳሉት ድርጅቱ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸውን ግለሰቦች በተለያየ ጊዜ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ወደ ሥራ እንዲገቡ ያደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ለ55 ሰዎች ስልጠና በመስጠት ላይ ነው።

የንግድ ክህሎት፣ የገንዘብ አያያዝ፣ የሥራ ፈጠረና መሰል ጉዳዮች በስልጠናው የተካተቱ ሲሆን በቀጣይም ሰልጣኞችን ወደ ሥራ ለማስገባት ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም