ለህዝብና ቤት ቆጠራው ህብረተሰቡ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ አስቀድሞ ማሳወቅ ያስፈልጋል ተባለ

56

አዲስ አበባ መጋቢት 8/2011  ለ4ኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ መሳካትና ህብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ እንዲሰጥ በዓላማውንና አስፈላጊነቱ አስቀድሞ ማሳወቅ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ህዝብና ቤት ቆጠራ የአሰልጣኞች ስልጠና ላይ የሚገኙ ባለሞያዎች ተናገሩ።

የአዲስ አበባ የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ከመምህራን፣ ከጤና እንዲሁም ከኮሚሽኑ ለተውጣጡ ለ413 ሲሰጥ የነበረውን የንድፈ ሐሳብና የተግባር ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰልጣኞች ስልጠና ተሳታፊዎች እንዳሉት የህዝብና ቤት ቆጠራ ለአንድ አገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፤ ይኸም እውን ሊሆን የሚችለው ህዝቡ የተሟላ መረጃ ሲሰጥ ነውና ለዚህ አስቀድሞ ለህዝቡ ማሳወቅ ለስኬታማነቱ ጉልህ ሚና አለው።

ለአብነትም ሰው ብሔሩን ሲጠየቅ አልሰጥም የሚል ምላሽ እንደሚሰጥ የተናገሩት ተሳታፊዎቹ ተጠያቂው ተፈላጊውን መረጃ እንዲሰጥ ገና መሰራት የሚገባቸው ስራዎች አሉ ይላሉ።  

አቶ ተመስገን ጫኔ ስልጠናው በንድፈ-ሀሳብና በተግባር የተደገፈ እንደመሆኑ በስልጠናው ወቅት ባደረጉት የመስክ ምልከታ ህብረተሰቡ ስለ ስቆጠራው ዓላማና አካሄድ ያለው ግንዛቤ ባለማደጉ የሚጠየቀውን መረጃ ለመስጠት እንደሚያመነታ ተናግረዋል።

አያይዘውም የተሰጠው ስልጠና በቆጠራው ላይ ለሚሳተፉት በቂ ቢሆንም ህብረተሰቡም ሲጠየቅ ተፈላጊ መረጃ እንዲሰጥ በሚዲያና በተለያየ የግንዛቤ ማስጨበጫ መንገዶች ስለቆጠራው ቀድሞ ማሳወቅ ያስፈልጋል ብለዋል። በቀሪ ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ቢሰራ የሚል ምክረ-ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። 

መምህርት ዘውድነሽ መለሰም ስልጠናው ወደ ትግበራ ሲገባ የሚተኮርባቸውን፣ ሊገጥሙ ከሚችሉ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎችን በተግባር በማስደገፍ መሰጠቱን አድንቀው፤ ከመስክ ምልከታው አንዳንዱ "ለምን እንቆጠራለን?"፤ "እሰከ ዛሬስ የት ነበራችሁ?"፤ "መቆጠር አንፈልግም" እና ሌሎች ምላሾችን እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ ለቆጠራው ስኬት ስለሚያስቸግር ህዝቡ ቆጠራ ለሚያካሂደው አካል ለተጠየቁት መጠይቅ ግልፅ ምላሽ መስጠት እንዲችሉ ከቆጠራው ዓላማና ከአስፈላጊነቱ አንፃር ኮሚሽኑ ቀሪ ስራዎችን መስራት አለበት ብለዋል።

ቆጠራው ከተጀመረ በኋላ ክፍተት እንዳይፈጠርም በተለያየ መንገድ ለህዝቡ ቀድሞ ማስገንዘብ እንደሚገባ መምህርት ዘውድነሽ ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ቴክኒክ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ኃይሉ ስልጠናው በዋናነት ለቆጠራው የሚያስፈልግ ብቃት እንዲኖራቸው፣ ለቆጠራው በተዘጋጀው የመረጃ አሞላል ስርዓት እንዲሁም ምን ጠይቀው ምን ምላሽ ማግኘት እንደሚችሉና እሱንም  ወደ መተግበሪያ ታብሌት እንዴት ማስፈር እንዳለባቸው በሚሉት ነጥቦች ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም ከመጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ13 ቀናትም በየክፍለ ከተማዎቹ ተመሳሳይ ስልጠና ለቆጣሪዎች እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።

ቆጠራው ታብሌቶችን በመጠቀም የሚከናወን መሆኑና ሂደቱም በተግባር ስልጠና መደገፉ ለመረጃ አያያዝና ከአሁን በፊት ከነበሩት ክፍተቶች ያድናልም ተብሎለታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም