በዞኑ የአፕል ችግኝ የሚያባዙ አርሶ አደሮች የገበያ ችግር እንደገጠማቸው ገለጹ

126

ደብረ ማርቆስ  መጋቢት 8/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን የአፕል ችግኝ በማባዛት ሥራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በገበያ ትስስር እጥረት ምክንያት የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ቅሬታቸውን ገለጹ።

በስናን ወረዳ የገዳማዊት ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አለቃ አለማየሁ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአፕል ችግኝን አባዝተው እየሸጡ ቢሆንም በገበያ ትስስር እጥረት ምክንያት ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም።

በዘርፉ መሰማራት ከጀመሩ ስድስት ዓመት እንደሞላቸው ጠቁመው የገበያ ትስስር የተሻለ በነበረበት ወቅት አንዱን ችግኝ ከ35 እስከ 40 ብር በመሸጥ የተሻለ ገቢ ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገበያ ትስስሩ እየቀነሰ በመምጣቱና የጥራት ደረጃው ያልተረጋገጠ የአፕል ችግኝ በነጋዴዎች በመቅረቡ በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ያዘጋጁት ከ8 ሺህ በላይ የጥራት ደረጃውን ያሟላ የአፕል ችግኝ ቢኖራቸውም በገበያ እጦት ምክንያት ለኪሳራ እዳረጋለሁ የሚል ስጋት እንደገባቸው ጠቅሰዋል፡፡

የገበያ እጦት ስጋቱን የሚጋሩት ሌላዋ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዘመናይ ብናልፍ በበኩላቸው ቀደም ባሉት ጊዜያት ምርታቸውን በአካባቢያቸው ያሉ አርሶ አደሮችና መንግስት በጨረታ ይረከቧቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የገበያ ተስስር ባለመፈጠሩና ገበያው በመቀዛቀዙ አባዝተው ያዘጋጁት የአፕል ችግኝ ገዢ ያጣል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

በተለይም ህገ ወጥ ነጋዴዎች ጥራቱ ያልተረጋገጠ ችግኝ ሲያቀርቡ ክትትል አለመደረጉ እንዲሁም "ችግኙ ብዛት ስለሌለው በጨረታ ለመግዛት አይመችም" በሚል ሰበብ ከሌላ ቦታ ተገዝቶ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ አመልክተዋል።

በእዚህም ህጋዊ ፈቃድ ይዘውና በግብርና ባለሙያ ታግዘው ያለሙትና ቀደም ሲል ከ20 እስከ 25 ብር ይሸጡት የነበረውን አንድ የአፕል ችግኝ ልፋታቸውን በማይተካ ሁኔታ ከ5 እስከ10 ብር ድርስ መሸጣቸውን ተናግረዋል።

"በመሆኑም በህገወጥ ንግድ ተሰማርተው ጥራቱን ባልጠበቀ መንገድ ችግኝ የሚያቀርቡትን መንግስት ሊቆጣጠርልንና ላለማነው ችግኝ  በድርጅትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የገበያ ትስስር ሊያጠናክርልን" ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ አትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ ሞላ ሰውነት በበኩላቸው እንዳሉት አርሶ አደሮች የአፕል ችግኝ በማባዛት እራሰቸውን እንዲችሉና ለሌሎችም እንዲያቀርቡ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

በተለይ አፕል አምራች በሆኑት በስናን እና ቢቩኝ ወረዳዎች በማህበር ተደራጅተው በብዛት እንዲያመርቱና ለገበያ እንዲያቀርቡ ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

"አልምተው ለገበያ የሚያቀርቡትን የተከተበ ችግኝም በየወረዳው በጀት ተይዞ እንዲገዛ እና ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጭ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

አርሶ አደሮቹ በገበያ ትስስር የሚያነሷቸው ችግሮች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሞላ በአሁኑ ወቅት ለመንግስት ግዥ እንዲመች በአንድ ማህበር ስም አድርጎ ምርታቸውን ለመግዛት መወሰኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሮች ትርፍ ችግኝ አለን ብለው ካሳወቁ እጥረት ያለባቸው ወረዳዎች ከሌላ ቦታ ከመግዛታቸው በፊት ከአርሶአደሮቹ እንዲገዙ የሚደረግ መሆኑን አስርደተዋል።

ችግኝ በህገ ወጥ መንገድ እየቀረበ ነው የተባለው ቅሬታ ከእውነት የራቀና ህጋዊ ፈቃድ ወስደው ከሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች የሚቀርብ መሆኑንም ባለሙያው አመልክተዋል።

አርሶ አደሮች ዋጋ ከፍ አድርገው መሸጣቸውና ተጠቃሚውም በተመጣጠኝ ዋጋ የሚሸጥለትን ፈልጎ በመግዛቱ የተፈጠረ የገበያ እጥረት መሆኑንም ባለሙያው አስረድተዋል።

በዚህ ዓመት በዞኑ አርሶ አደሩን በአፕል ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ከ570 ሺህ በላይ ችግኝ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ባለው ከ280ሺህ በላይ  ችግኝ ለማዘጋጀት ተችሏል።

በአፕል ልማቱም በዞኑ ከ10 በላይ ወረዳዎች አየተሳተፉ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም