ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የሸንኮራ አገዳ ያቀረብንበት ክፍያ አልተከፈለንም--የሸንኮራ አገዳ አብቃይ ማህበራት

198
ሰመራ ግንቦት 23/2010  ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ላቀረቡት ሸንኮራ አገዳ  ምርት ክፍያ ባለማግኘታቸው መቸገራቸውን በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ የሸንኮራ አገዳ አብቃይ  ማህበራት  ገለጹ፡፡ የፋብሪካው አስተዳደር  በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ከክልሉ  የስራ ኃላፊዎች ጋር ተቀራርበው እየሰሩ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በወረዳው የገበላይቱ ሸንኮራ አገዳ አብቃይ ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዩሱፍ አሊ  እንዳሉት ባላቸው ግማሽ ሄክታር መሬት በዓመት ሁለት ጊዜ የተለያየ ሰብል በማልማት በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ የክልሉ መንግስት የተሻለ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ  ባለን  መሰረት ከ2007  ጀምሮ በሸንኮራ አገዳ አብቃይ ማህበራት ተደራጅተው ወደስራ በመግባት በ2008 ዓ.ም በ60 ሄክታር መሬት ላይ  ሸንኮራ አገዳ አልምተው  ለፋብሪካው  አቅርበው እንደነበር  ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ላቀረቡት ምርት  እስካሁን  ክፍያ ባለማገኘታቸው እሳቸውም ሆኑ ሌሎች የማህበሩ አባላት ከነቤተሰቦቻቸው  ለችግር መጋለጣቸውን አመልክተዋል፡፡ የሸንኮራ አገዳ ልማት ስራው በመቆሙም  መሬቱ በመጤ አረም እየተወረረ መሆኑንም ተናግረዋል ሌላው የሽንኮራ አገዳ አብቃይ ማህበር አባል አቶ መሃመድ ኡመር በበኩላቸው ማህበሩ ወደሸንኮራ አገዳ ልማት በ2007ዓ.ም በመግባት  በ122 ሄክታር ላይ መስኖን በመጠቀም  በሸንኮራ አገዳ ተክል ቢሸፍኑም ባጋጠማቸው የውሃ እጥረት  እንደተበላሸባቸው  ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ  ፋብሪካው  የስራውን ውል በማያውቁት ምክንያት  በማቋረጡና ማልማት ባለመቻላቸው ከ280 በላይ የማህበሩ አባላት ያጋጠማቸውን ችግር እንዲፈታላቸው ለፋብሪካውና ለክልሉ የሚመለከተው አካል ቢጠይቁም መልስ የሚሰጣቸው ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ እሳቸውም ሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በግፊት ሳያምኑበት ወደሸንኮራ አገዳ  ልማት እንዲገቡ መደረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ  በወረዳው የሞሚናከሌ ሽንኮር አገዳ አብቃይ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ኖራ ኢብራሂም ናቸው፡፡ የመሬት ዝግጅት ስራው ሲከናወን ያለበቂ ሁኔታ በችኮላ በመደረጉ ቦዮች ውሃን የመሸከም አቅም ስላልነበራቸው ተበላሽተው በ2008ዓ.ም. በማህበሩ በ50 ሄክታር ይዞታ  ላይ ተተክሎ የነበረ  ሽንኮራ አገዳ በውሃ እጥረት መድረቁን አመልክተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ልማቱ ቆሞ ከ100 በላይ የማህበሩ አባላት ማገኘት የሚገባቸውን ጥቅም ከማጣታቸውም በላይ ችግሩን ለመፍታት ያደረጉት ሙከራ የፋብሪካው  አመራሮች በየጊዜው መቀያየር ምክንያት እንዳልተፈታላቸው ገልጸዋል፡፡ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ  ተወካይ አቶ ነጋሲ ሃለፎም ስለጉዳዩ በሰጡት ምላሽ ስራው  ህብረተሰብ ከፋብሪካው ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ ቢጀመርም በውሃ ቦዮች ብልሽትና  በ2008ዓ.ም በነበረው ድርቅ ምክንያት ያጋጠመው  የውሃ እጥረት የማህበራቱ ብቻ ሳይሆን የፋብሪካውም አገዳም ጭምር መቃጠሉን ተናግረዋል፡፡ ይህም ሆኖ ስራው ያለበቂ ጥናት በመጀመሩ  በፋብሪካው ላይ ከፍተኛ ኪሳራ በመድረሱ ውሉን አቋርጦ የማህበራቱ መሬት በፋብሪካው ወጪ ተዘጋጅቶ እራሳቸው የሚያዋጣቸውን ሰብል እንዲያለሙ ባለፈው ዓመት ቢሞከርም ማህበራቱ ፍቃደኛ ባለመሆናቸውን አለመሳካቱን ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን  በማህበራቱና በፋብሪካው መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው  የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተቀራርበው እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ማህራት ማደራጃና ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ነኢማ መሃመድ በበኩላቸው በማህበራቱና  በፋብሪካው መካከል ያለውን አለመግባባት እልባት ለመስጠት በተደጋጋሚ ቢሞከርም  የፋብሪካው አመራሮች በየጊዜው ስለሚቀያየሩ መጓተቱን አመልክተዋል፡፡ ይሁንና አሁን ካሉት የፋብሪካው አመራሮች ጋር ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየተወያዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዱብቲ ወረዳ ከ2ሺ በላይ አባወራዎችን አቅፈው የሚንቀሳቀሱ 16 የሸንኮራ አገዳ አብቃይ ማህበራት እንደሚገኙ ኃላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም