በጉድሩ ወረዳ ሆስፒታል ተገንብቶ ለአገልግሎት በቃ

66

ነቀምቴ መጋቢት 7/2011 በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ጉድሩ ወረዳ የተገነባው ሆስፒታል ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

ሆስፒታሉን መረቀው ስራ ያስጀመሩት የአሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንትና የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተተባባሪ ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን ናቸው፡፡

በምረቃው ስነስርዓት ወቅት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደተናገሩት ሆስፒታሉ የተገነባው የክልሉ መንግስት በመደበው ከ56ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ነው፡፡

ሆስፒታሉ የተመላላሽ ህክምና ፣  ተኝቶ የማከም፣ የራጅ ፣የቤተ ሙከራ፣ የቀዶ ህክምና የወሊድና ሌሎችንም አገልግሎቶችን አካቶ መያዙን ገልጸዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎችና የህክምና መሳሪዎች የተሟሉለት መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ደረጄ  ሆስፒታሉ ለአምስት ወረዳዎች እና አጎራባች አካባቢዎች ጨምሮ  ከ400ሺህ በላይ ለሚበልጥ ህዝብ እንደሚያገለግል አስታውቀዋል፡፡

ወይዘሮ ጠይባ በበኩላቸው የሆስፒታሉ መገንባት የአካባቢው ህዝብ የጤና አገልግሎት ችግር እንደሚፈታ ገልጸው  ህብረተሰብም የራሱ ሀብትና ንብረት መሆኑን  ተገንዘቦ ሊጠብቀውና ሊንከባከበው  እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሆስፒታሉ ጤና ባለሙያዎች ለህዝቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የሙያ ግዴታቸውን  መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የሆስፒታሉ መገንባት የአካባቢው ህብረተሰብ ቀደም ሲል ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሻምቦና አምቦ ጭምር ለመሄድ  ይገደድ የነበረውን ችግር  እንደሚያቃልል ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም