የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ማጠናከሪያ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በነቀምቴ ተካሄደ

85

ነቀምቴ መጋቢት 7/2011 ለኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን እንቅስቃሴ ማጠናከሪያ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በነቀምቴ ከተማ ተከፈተ።

መርሐ ግብሩ ለ10 ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ከ1ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢም ይጠበቃል።

የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ኃላፊ ወይዘሮ አስካለ ለማ እንደተናገሩት ፌዴሬሽኑ መርሐ ግብሩ የክልሉን ሴቶች ገቢያቸውን በማሳደግ ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግን ዓላማ ያደረገ ነው።

በክልሉ የነበረው የሰላም እጦት ነጋዴዎች ተንቀሳቅሰው ሥራቸውን እንዳያከናወኑ ማድረጉን አስታውሰው፣በአካባቢዎቹ አንጻራዊ ሰላም በመፈጠሩ የንግድ፣ትርዒትና ባዛር መከፈቱን ተናግረዋል።

መርሐ ግብሩ ፌዴሬሽኑ ሴቶች ከጠባቂነት ወጥተው ራሳቸውን ለማስቻል እንደሆነም አመልክተዋል።

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ደራርቱ ያደሳ መርሐ ግብሩ በከተማው የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ያመላክታል ይላሉ።

መርሐ ግብሩ  የቤት ቁሳቁስን የሚያካትቱ  ምርቶችን  በቅናሽ ዋጋ ለመግዛት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ መርካቶ መምጣታቸውን የገለጹት አቶ ብርሃኑ መሐመድ በከተማው የተከፈተው የንግድ፣ ትርዒትና ባዛር ነጋዴውንና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እምነታቸውን ገልጸዋል።

በፈሳሽ ሳሙና ንግድ ላይ የተሰማሩትና  ከአዲስ አበባ የመጡት አቶ መሐመድ ኢሳ በበኩላቸው  መርሐ ግብሩ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ በአገር እድገት ውስጥ ሚናው ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ ከ150 በላይ ነጋዴዎች እየተሳተፉበት ሲሆን፣ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም