የተቋማት ግንባታን በአገራዊ እሴት መቃኘት

288

ሰለሞን ተሰራ (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለዘመናት ከሥርዓት ወደ ሥርዓት ስትሸጋገር የገጠሟት ሕመሞች ይታከሙ የነበሩት በማስታገሻዎች እንጂ፣ ዘላቂ ፈውስ በሚያመጡ መድኃኒቶች አልነበረም። መድኃኒቶቹ ጠንካራ ተቋማት መሆን ሲገባቸውና በሕግ ማዕቀፍ መመራት ሲኖርባቸው፣ በግለሰቦችና ቡድኖች ፈቃደኝነት መገንባታቸውና መፍረሳቸው በአገር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል፡፡

አለም አቀፉ ማህበረሰብ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በመመደብ ታዳጊ አገሮችን አሳታፊ፣ ተጠያቂና ውጤታማ የሆኑ ተቋማትን ለመገንባት የሚያደርጉትን አታካች ጥረት ይደግፋል።

ማሻሻያው "የተሻሉ ተቋማትን ለመገንባት ያስችላል" የሚል እምነት ያሳደረ ነው። ተቋማቱም የህግ የበላይነትን በማስፈን፣ ኢኮኖሚውን በመደገፍ እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን በማዳረስ ድህነትን ለመቀነስ እንደሚያግዙ ይገመታል። ይህም ልማትና እድገቱን ቀጣይነት እንዲኖረው ያደርጋል።

በመሰረቱ የተሻሉ ተቋማትን መገንባት ቀላል ስራ እንዳልሆነ እሙን ነው። በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአብዛኛው የሚደረጉት ጥረቶች የተቀመጠላቸውን ግብ ከማሳካት አኳያ  ክፍተት አለባቸው። በተቋማት ግንባታ ከፊት የተሰለፉት ለጋሽ አገሮች ለፕሮጀክቶቹ  ከፍ ያለ ገንዘብና ባለሙያ ቢመድቡም የሚገኘው ውጤት የተደበላለቀ ነው።

የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ተቋማት ማለትም ምርጫ ቦርድ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ተፅዕኖ ነፃ ወጥተው በገለልተኝነት መደራጀታቸው እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ከእነዚህ ተቋማት በተነፃፃሪነት ከዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በስተቀር ብዙዎቹ በመሽመድመዳቸው የደረሰውን ችግር አገር ያውቀዋል፡፡ የሕግና የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነቱ በመጣሱና የአስፈጻሚው ተላላኪ በመደረጉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ እንደ ውኃ ጠምቶታል፡፡

ጥናቶች እንደሚያሳዩት የዚህ ውድቀት ዋጋ  ጥልቅ ሲሆን፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለድህነት፣ ለጥቃት፣ ለግጭት እና በመንግስታት ላይ  የመፍረስ አደጋ ያስከትላል። በተጨማሪ ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ይገዳደረዋል ።

እናስ ስኬታማ ለመሆን ምን ማድረግ ይገባል?

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት የተሻሉ ተቋማት ምን አይነት ጠቀሜታ እንዳላቸው መገንዘብ አስፈላጊ ነው ። ዲሞክራሲ የሰፈነባቸውና ሰላማዊ ማህበረሰብ የገነቡ አገሮች ልምድ የሚያሳየው ይህንኑ ነው ። ያም ቢሆን የአደጋ ስጋት የተደቀነባቸው አገሮች ተቋማት የተዘበራረቀ አሰራር ከዚህ በተቃራኒ የቆመ ነው።

የጨዋታው ደንብ

በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ከተመለከትነው የመንግስት ተቋማት ማህበረሰብንና ድርጅቶችን በማቃናት “የጨዋታውን ደንብ” የማስተካከል የማይተካ ሚና አላቸው።

እነዚህ ደንቦች ኢኮኖሚውንና ፖለቲካውን በማቃናትና በማሳለጥ እቃዎችና አገልግሎት እንዴት ተደራሽ እንደሚሆኑ እንዲሁም በጀት እንዴት አገልግሎት ላይ እንደሚውል እና የፍትህ ስርአቱን አተገባበር ይወስናሉ።ነገር ግን እነዚህ ደንቦች ብቻቸውን ውጤታማ መሆን አይችሉም።

ደንቦች በውጤታማና ታማኝ ተቋማት ካልተደገፉ በስተቀር የሐብት ብክነት ከማስከተል ያለፈ ጠቀሜታ የላቸውም። የሚሰጠው አገልግሎትም  በአግባቡ የማይዳረስ ሲሆን ሰዎችም ተገቢውን ጥበቃ አያገኙም ። ተግባራዊ ጥናቶችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው ። የአለም ባንክና የተባበሩት መንግስታት ጥናት እንደሚያሳየው የተቋማት አደረጃጀት በተለያዩ የማህበራዊ ኢኮኖሚ እይታ ለድህነት ቅነሳ ከፍተኛ እገዛ ያበረክታሉ።

የተቋማት ተጠናክሮ መውጣት መሪዎች አገርን በሥርዓት እንዲመሩ፣ ሥልጣናቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖርበት፣ ከአንድ አሠራር ወደ ሌላ ሲሸጋገሩ በነሲብ ሳይሆን በሕግ ብቻ እንዲመሩ ይረዳል፡፡

ዪ ፌንግና ጃኒ አሮንስ ( Feng, Yi, Democracy, Governance, and Economic Performance: Theory and Evidence, Massachusetts Institute of Technology, Cambridge, MA, 2003; and Aron, Janine, Growth and Institutions: A Review of Evidence, The World Bank Research Observer, 2000 )ተቋማት ለኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ በተመለከተ ምልከታቸውን ያስቀመጡ ሲሆን፤  የአለም የልማት ሪፖርት (World Bank, Economic Growth in the 1990s: Learning from a Decade of Reform, 2005;) በበኩሉ ደካማ ተቋማትና ግጭት ያላቸውን ትስስር በማስቀመጥ ውጤታማ ያልሆነ መንግስት ከፍተኛ ብጥብጥ የማስተናገድ እድሉ ሰፋ ያለ መሆኑን አሳይተዋል።

ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች ያስቀመጡት መከራከሪያ ጠንካራ ተቋማት "ለምን አስፈላጊ ናቸው?" የሚለውን የሚያሳዩ ናቸው። ከዚህ ባለፈ ለጋሽ አገሮች ለተቋማት ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ መለስ ብለው እንዲመለከቱ ከማስቻሉ ባለፈ ለጋሾቹ  ትክክለኛውን የጨዋታ ህግ በመቅረጽ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ተፈጻሚ እንዲያደርጉ እንዲደገፉ ይረዳል።

አለም አቀፉ ማህበረሰብ ውጤታማ ተቋማትን ለመገንባት የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተ የተሰበሰበው መረጃ አስገራሚ መሆኑ ተጠቅሷል። በዚህም ተቋማቱ በዚያ ያሉ ውድቀታቸውን የሚያሳዩ ውጤቶችንም አስቀምጠዋል። ለጋሾቹም የቀደመ ጉድለታቸውን የተረዱት ሲሆን፤ የሚያቀርቡት ውጤት የተደበላለቀና አንገት የሚያስደፋ ናቸው።

ማት አንድሬወስ , (The Limits of Institutional Reform, 2013 ) በሚለው ጽሁፋቸው እነዚህን እጥረቶች አስመልክቶ በቂ ማሳያ አስቀምጧል። ማት ባስቀመጠው ትንታኔ መሰረት ግለሰቦች ለተቋማት ማሻሻያ ፕሮጀክቶች የሚያደርጉት ጥረት ስኬት 50 በመቶ  ነው ይላል።በመላምቱ ብዙ አገሮች የተቋማት ማሻሻያን የሚጀምሩት በለጋሽ አገሮች ድጋፍ ላይ ተመርኩዘው በመሆኑ ለውጥ የማምጣት እድላቸው የተመናመነ ነው ይለናል።

ለዚህም ማሳያ ኡጋንዳን ያቀርባል ። የኡጋንዳ መንግስት ባለፉት አስርት አመታት የተለያዩ የተቋማት አደረጃጀቶችን ብትከተልም  አንድሪው እና ባቴጌካ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ጥናት ወረቀት ላይ  ( Overcoming the limits of institutional

reform in Uganda) እንዳስቀመጡት የፈጠሩት ተጽእኖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

እናስ ይህንን እጥረት ለማቃለል ለምን አዳገተን?

በመጀመሪያ የምንከተለው አቀረራብ ተሰፍቶ የተሰጠንን ነው። ለውጡን ስንጀምር የተለመዱትን ሞዴሎች በመከተል የመፍትሄ አማራጭ የምናደርጋቸው የተሻሉ የምንላቸውን እነዚህን ውጤት አልባ ትንታኔዎችና መደምደሚያዎች ነው።

የምናከናውነው ተግባር አዋጪ አለመሆኑንን ብንገነዘብም አካሄዳችንን ሳንለውጥ የምዕራባውያንን የተለመዱ ሞዴሎች በመከተል ውድቀታችንን እናጠናክራለን። በብዙ መልኩ ጥናቶች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው ። አሁን ላይ ብዙ ጥናቶች ውጤታማ ተቋማትን ለመገንባት የተለያዩ መንገዶችን መከተል አዋጪ መሆኑን  በማሳየት የምዕራባውያንን መንገድ ሙጭጭ ማለት እንደማያስፈልግ ይጠቁማሉ ።

የዚህ ምክንያት ደግሞ የተቋማት ግንባታ በነባራዊ ሁኔታዎች የተቃኘና ተቋማትን በተመለከተ የሚነሱ አጠቃላይ ሐሳቦች ማካተት እንዳለባቸው ነው ። ነጠላ ሀሳብ ዘመናዊ ተቋማትን ለመገንባት በቂ አለመሆኑ ግልጽ ወጥቷል።ይህንን ሀሳብ በበሰለ መንገድ በመተንተን ብቃትን መሰረት በማድረግ ለስራችን መነሻ ማድረግ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው።

ይህ ደግሞ ወደ ሁለተኛው ፈታኝ ጉዳይ ይመራናል፤ ማሻሻያውን በአገራዊ እሳቤ መቃኘት። ነባራዊ አገራዊ ሁኔታዎች የሚያሳድሩት ተጽእኖ ለማንም የተደበቀ ባይሆንም አለም አቀፋዊ ሞዴሎችን በመከተል  ማሻሻያ ለማድረግ መነሳት አገራዊ እሳቤዎቸን ወደ ኋላ መተው  ማለት አለመሆኑንም መገንዘብ ግድ ነው ።

እሳቤዎቹ ፖለቲካዊ፣ባህላዊ ወይም ማህበራዊ ቢሆኑም በአብዛኛው ትኩረት የተነፈጉ በመሆናቸው የሚገኘው ውጤት ተመሳሳይ ነው። ከልክ ያለፈ ጉጉት ማሳደር ፕሮጀክቶቹን ራዕይ አልባና ደካማ ግብ ያላቸው በማድረግ የተቋማቱን ግንባታ ውስብስብ ያደርገዋል።

የኡጋንዳን ምሳሌ በድጋሚ ከተመለከትነው የተደረጉት ማሻሻያዎች አዲስ ህግ እንዲወጣ አስገድደዋል።በዚህም አዳዲስ የመንግስት አስፈጻሚ ተቋማት ተቋቁመዋል ። ነገር ግን አካሄዱ መሰረታዊ ባህሪያትን (ሙሰኝነት) የዘነጋ ሲሆን፤ የአስፈጻሚ አካላቱን  ጠቃሚ ነባራዊ ሁኔታ አላስቀመጠም።

በኢትዮጵያም በልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ፍልስፍና የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ መጠን ያለው የአገር ሀብት እያገላበጡ፣ በአገር ላይ የደረሰው ጉዳት ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት የጎደለውና ተጠያቂነት ስሌለበት የአገር ሀብት እንዴት እየባከነ እንደሆነ፣ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን ሪፖርቶች ማገላበጥ በቂ ነው፡

ይህ ማለት ደግሞ ሰዋዊ የሆኑ እሳቤዎች አልተካተቱም ማለት ነው ። ተቋማት የሰዎች ስብስብ በመሆናቸው በተቀመጡ የመነሻ ሐሳቦች በመታገዝ እንደ ማሽን ለመስራት ከመጣር ይልቅ የሰዎችን ፍላጎት፣ ልማድ፣እምነት እና ጉጉት በማካተት ተግባራዊ መደረግ አለባቸው ። እነዚህን ሰዋዊ አላባዎች ከዘነጋናቸው ለተቋማት ግንባታ ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦችን በማጉደል ሙሉ ነው ልንል አንችልም።

ራትሜል የተባሉ ምሁር ( Rathmell, A., Fixing Iraq’s Internal Security Forces. Why is Reform of the Ministry of Interior so Hard?, 2007)  በሚል ርእስ በኢራቅ እና አፍጋኒስታን ያለውን የተቋማት ግንባታ አስመልክተው ባሰፈሩት ጽሁፍ  ጠንካራ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የተቋማትን ማሻሻያ እርምጃ ይገዳደራል ።

በምስራቅ አውሮፓ ያለው የተቋማት ባህላዊ አደረጃጀት ወይም ሁኔታ ሰዎች በባህሪያቸው የሚጠብቁትን ነገር እና ለማሻሻያው  የሚሰጡትን ምላሽ ያሳያል ይሉናል። ምላሹ ምንም ይሁን ምንም ለተቋማት ግንባታ የግለሰቦችና የድርጅቶች ይሁንታ አስፈላጊ መሆኑን ያሳየናል።

ከላይ የተጠቀሱት አስቻይ ሁኔታዎች ለመረዳት አዳጋች ቢመስሉም እውነታው ግን ይህ ነው። አንድን ተቋም ልክ እንደ በረዶ ቋጥኝ ብንመስለው አስቻይ ሁኔታዎቹ የሚገኙት ከውኃው ስር ነው፤ እናም በጣም ጠልቀን ካልገባን ልናያቸው አንችልም።ይህም ወደ ሶስተኛው ፈታኝ ሁኔታ ያሸጋግረናል፤ በሽታውን በማከም አገራዊ የሆነ ለውጥ ማስመዝገብ።

አሁን ላይ የምንከተላቸው አቀራረቦች በአብዛኛው የኤክስፐርቶችን እውቀት የሚያስቀድሙ  ናቸው። እነዚህ ኤክስፐርቶች ደግሞ በአብዛኛው የሚገኙት የኢኮኖሚና የልማት ትብብር በሚያደርጉ አገሮች ተቋማት ውስጥ ነው።ባለሙያዎቹ የሚያቀርቡት የመፍትሄ ሃሳብ ወይም ማሻሻያ ያላቸውን ሙያዊ ልምድ መሰረት ያደረገና የአለምን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው።

ይህ አቀራረብ ደግሞ ውስብስብ የሆነ ከባቢ ሁኔታ ላላቸው አገሮች በጣም አሻሚና ብዛት ያላቸው የማይታወቁ  እውነታዎችን ያዘሉ በመሆኑ ትንታኔውን በቀላሉ ለመረዳት ያዳግታል። የተቋማት ግንባታ በውስብስብነቱ የታወቀ ሲሆን፤ ኤክስፐርቶች የአካባቢውን ማህበረሰብ እሳቤዎች በማካተት መስራት ይጠበቅባቸዋል።

በአገራዊ እሳቤ ተጠቃሚ የሚሆኑት  እውነተኛዎቹ ኤክስፐርቶች የሚገኙት ደግሞ በተጠቃሚ ተቋማት ውስጥ ነው። አገራዊ እሳቤዎችን ከማንም በተሻለ መንገድ ከተገነዘቡት ማሻሻያው ምን ያህል ተጽእኖ ማሳደር እንደሚችልም በደንብ ይረዱታል።

አገር በቀል ባለቤትነት ዘርፈ ብዙ መልክ አለው። ለውጥ በሚከናወንበት ተቋም ውስጥና ውጭ ያሉ ግለሰቦችንም ያካትታል። ግለሰቦቹ በሽታውን በመፈተሽ፣ ጠቃሚ አገር በቀል እርምጃዎችን በመለየት እና የአተገባበር መፍትሄ በማስቀመጥ ረገድ ቁልፍ ሚና ያላቸው ናቸው።

እነርሱ የሚለውን እሳቤ አጥብቦ መመልከት  የሚያበረክቱትን  የለውጥ እገዛ  በማቃለልና ከሚመጣው  መሻሻል እጠቀማለሁ የሚለውን ተነሳሽነታቸውን በመገደብ  ከሚገኘው ውጤት በባለቤትነት ተጋሪ እንዳይሆኑ መገደብ ነው።

አስፈላጊ የሆኑ የለውጥ እርምጃዎች

በመጠኑ የጠቃቀስናቸው ተግዳሮቶች ስኬትን የማደናቀፍ አቅማቸው ላቅ ያለ ነው ። እነዚህን መሰናክሎች እንዴት ማስወገድ እንችላለን?

በቅድሚያ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ያላቸው አገር በቀል "የቴክኒክ እውቀት ዝቅተኛ ነው" የሚለውን አመለካከት በማቃለል ለስኬቱ በጋራ መረባረብ ይገባል። የተቋማት ግንባታ ውስብስብ በመሆኑ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ኤክስፐርቶች ብቻቸውን ሊያከናውኑትም እንደማይቻሉ መዘንጋት የለበትም።

ከላይ የተጠቀሰውን ማሳያ  ከተቀበልን ዘንዳ ስራችን በተፈጥሮው ጥልቅ የሙከራ ሂደቶችን ማለፍ እንዳለበት እናውቃላን።ለዚህ ስኬታማነት ደግሞ የተለያዩ ጥቃቅን ደረጃዎችን በማለፍ ወደ ጥቅል ድምዳሜ መምጣት ይገባል።

በመቀጠል የለጋሾቹን የሙከራ ሂደት ለመደገፍ አለን ከሚሉት ተለምዶአዊ ሞዴል በመውጣት ችግር ፈቺ ሃሳብ ማመንጨት ይጠበቅብናል። ችግሮች ሌሎች አማራጮችን ለማየት ቀዳዳ የሚከፍቱ በመሆኑ ከግንዛቤ መክተት ያስፈልጋል። ይህን ስንል ደግሞ ችግሮችን ለመለየት ኤክስፐርት ያስፈልገናል ማለት አይደለም።

በአንጻሩ የተፈጠሩትን ችግሮች ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር በማስተሳሰር ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል። በጋራ ችግሮቹን መለየት ከተቻለ  ለውጥ ለማምጣት የሚያግዙ ድምዳሜዎች ላይ መድረስ ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ የችግሮቹን ምንጭ በመለየት መፍትሄ ለማበጀት ይረዳል። የተፈጠሩትን ክፍተቶች በጥንቃቄ መለየትና መተንተን  ከተቻለ የመፍትሄ አቅጣጫውን ያመላክቱናል።በተለምዶ የተቋማትን ድክመት በመለየት የምናውቀውን ማስተካከያ ለማስቀመጥ የምናደርገው ተለምዶአዊ አካሄድ ጊዚያዊ ጥገና ከመስጠት ያለፈ ዘላቂ ጠቀሜታ የለውም።

ሶስተኛው  እርምጃ በተቋሙ ላይ ጥቅም ያላቸው ግለሰቦችን በኤክስፐርት እሳቤ በሙሉ ልባችን ካሳተፍናቸው የልማት ተዋናዮች ከእነርሱ ጋር በመተባበር ለውጡን እውን ማድረግ ይችላሉ።ይህ ማለት ደግሞ ዙሪያ መለስ በሆነ መልኩ ለተቋማቱ ይሁንታ በመስጠት አብሮ በመስራት እና መፍትሄ በመፈለግ ለውጥ ለማምጣትና መወሰድ ስላለበት እርምጃ ለማመላከት ያግዛል።

ውጤታማ፣ ተጠያቂ እና አሳታፊ ተቋማትን የመገንባት ሂደቱ ልክ እንደ ስዕል ቅብ የሚታይ ነው። በምዕተ አመቱ የልማት ግብ ላይ የተቀመጠው 16 ኛ ተግባር እንደሚያሳየው የተቋማት ግንባታ ጠቃሚነቱ አጠያያቂ አይደለም።

ተቋማት ድህነትን በመቀነስ ሂደት ያላቸው ሚና የላቀ ነው። የፍትህ ስርአቱን በማሻሻል የኢኮኖሚ እድገቱን ያሳልጣሉ። የተለያዩ ደንቃራዎች ቢኖሩም የተባበሩት መንግስታ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ለማሳካት ለያዘው ተልዕኮም መሰረት ናቸው ።

ቀደም ብሎ እንደተገለጸው የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር እና የፍትህ እጦት ለሚባል በሽታዎች ዋና መፍትሄ ነው፡፡ ተቋም ሲባል ግን እምነት እሚጣልበት እና ቅንነት ያለው ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ለአንድ ተቋም ስብእና ማለት የልቀት፣ የታማኝነት እና ህጋዊነት መመዘኛዎችን አካቶ ለመልካም የስራ ባህሪ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚያሳየው ቁርጠኝነት ነው

ለዚህ ስኬት ግን መሰረታዊ የተባሉ እርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይላል። በቅድሚያ ካለፉት ተሞክሮዎች ትምህርት በመውሰድ ስራውን ለማከናወን አዲስ አስተሳሰብ ማዳበር ይገባል። የአስተዳደር ለውጥ፣የተቋማት ስነ ልቦና እና ቀና አስተሳሰቦች አዲስ ሞዴልን የሚፈልጉ ናቸውና።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም