የኩላሊት ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ የግንዛቤ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል ተባለ

73

አዲስ አበባ መጋቢት መጋቢት 7/2011 የኩላሊት ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ የቅድመ ጥንቃቄ ትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው ሊሰሩ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገለፁ።

አስተያየት ሰጪዎቹ መገናኛ ብዙሃንና በጤና ላይ የሚሰሩ ተቋማት ስለህመሙ እየሰሩ ያሉት የግንዛቤ ማሰጨበጫ ስራ በቂ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

በዓለም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል።

በኢትዮጵያ በአዝጋሚ የኩላሊት ድክመት ህመም ሳቢያ በየዓመቱ 2 ነጥብ 4 ዜጎች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ከኢትዮጵያ የኩላሊት ህመም ማህበር የተገኘ መረጃ ይጠቁማል።

በየጊዜው እየጨመረ ያለውን የኩላሊት ታማሚዎች ቁጥር ለመቀነስ ኅብረተሰቡ ስለበሽታው ምንነትና ማድረግ ስለሚገባው ቅድመ-ጥንቃቄ ማሳወቅ እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ስለህመሙ ያለው ግንዛቤ ካደገ ራሱን ከበሽታው ይከላከላል ያሉት አቶ ታዬ ከበደ ለዚህም የሚደረጉ የግንዛቤ ስራዎች በተከታታይነት ሊሰጡ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ስለሆነም ዋና ትኩረቱ መደረግ ያለበት ቅድመ-ጥንቃቄ ላይ በመሆኑ ችግሩ ከመፈጠሩና ለችግሩ ከመጋለጣችን በፊት ስለበሽታው አስከፊነት  ማስተማርና የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል።

አቶ ሰለሞን መዝሙርና ወይዘሮ ጽጌረዳ ከበደ በበኩላቸው ኅብረተሰቡ ነፃ የምርመራ አገልግሎትን በየጊዜው ማግኘት እንዳለበት ነው የተናገሩት።

በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪ ዶክተር ሶስና ኃይለማርያም እንዳሉት በአዲስ አበባና በክልሎች የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለማስፋት እየተሰራ ነው።

በተጨማሪም አስቀድሞ ለመከላከል ስራ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

ደም ግፊትና የስኳር ህመም፣ አልኮልን በብዛት መጠቀም፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግና ከመጠን ያለፈ ውፍረት    ለኩላሊት ህመም ተጋላጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ኅብረተሰቡ ወደ ህክምና ተቋም የሚሄደው ኩላሊቱ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዳ በኋላ በመሆኑ የመዳን ዕድሉን ያጠበዋል ያሉት ዶክተር ሶስና በየወቅቱ ምርመራ በማድረግ የኩላሊት ጤንነትን መጠበቅ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም