በገቢ አሰባሰብ የታዩ ክፍተቶችን ለማካካስ እየተሰራ ነው - ገቢዎች ሚኒስቴር

121

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2011 ባለፉት ሶስት አመታት በገቢ አሰባሰብ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማካካስ እየሰራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በአምስት ዓመታት 599 ቢሊዮን ብር እንዲሰበስብ የታቀደ ሲሆን በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ በታየው መቀዛቀዝና በነበረው አለመረጋጋት የዕቅዱን ያህል ሳይሰበሰብ ቆይቷል።

በሚኒስቴሩ የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መሐመድ አብዱ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት በሶስት አመት ተኩል ያለው አጠቃላይ የገቢ አሰባሰብ 79 በመቶ ነው።

ይህን አካክሶ በቀጣይ አንድ አመት የተፈለገውን ገቢ ለማሳካት ገቢ የመሰብሰብ አቅምን የማሳደግ ስራ በተቋሙ በኩል መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በአመቱ ከሚደርሰው የገቢ ድርሻ በላይ በማቀድና ግብር ከፋዩን በማንቀሳቀስ ገቢው ላይ ለውጥ እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አንፃር በዚህ አመት ባለፉት ስምንት ወራት ለአመቱ ከተያዘው አጠቃላይ ገቢ 86 በመቶ የሚሆነውን ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ2008 እስከ 2012 በሚቆየው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በገቢ ረገድ ይሰበሰባል ተብሎ የተያዘው 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ነው።

አቶ መሐመድ እንደሚሉት ገቢው ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ነው የገለፁት።

በእቅዱ ታሳቢ ተደርጎ የነበረው ኢኮኖሚ በሚፈለገው ልክ አለማደጉና በአገሪቱ ግብር መክፈል የሚገባቸው አካላት ሙሉ በሙሉ ወደ ግብር ስርዓት ባልገቡበት ሁኔታ ይህን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ ከባድ መሆኑን ተናግረዋል።

በእቅዱ የተቀመጠው ገቢ በጣም የተለጠጠ እንደሆነ ገልፀው ይህን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል ተስፋ አለመኖሩን ተናግረዋል።

የታቀደውን ገቢ ለመሰብሰብ ታሳቢ ተደርገው የነበሩ የኢንዱስትሪ፣ የኢንቨስትመንት የስራ እድልና የአምራች ዘርፍ በተፈለገው መልኩ ሽግግር ያልታየበት መሆኑ እቅዱ ላለመሳካቱ ሚና ያላቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በአፍሪካም ይሁን ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ዝቅተኛ ገቢ ከሚሰበስቡ ተርታ ኢትዮጵያ የምትሰለፍ መሆኗንም ነው ያነሱት።

በአገሪቱ የታየው አለመረጋጋትም  በኢኮኖሚው ላይ በፈጠረው ጫና መገኘት የነበረበት ገቢ እንዳይገኝ ተጨማሪ ምክንያት ነበር ብለዋል።

በሌላ በኩል ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት 40 በመቶ የሆነውን ድርሻ ከያዘው ከግብርናው ዘርፍ የሚገኘው ገቢ በመጠን አነስተኛ መሆኑም ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከዚህም ሌላ ግብር መክፈል ከሚገባቸው 40 በመቶ የሚሆኑት ወደ ታክስ ስርዓት ያልገቡ በሆኑበት ሁኔታ ላይ አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ብር መሰብሰብ እንደሚያዳግት ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ግብር የሚከፍለው 60 በመቶ ብቻ እንደሆነና በኢ-መደበኛና በህገ-ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩትን ወደ ግብር ስርዓቱ ማስገባት ቢቻል ግን የመሰብሰብ አቅም ይፈጥር እንደነበር ነው ያነሱት።

የሁለተኛው ዕቅድ ዘመን ገቢ ሲታቀድ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት የግብርን ድርሻ ከነበረበት 10 በመቶ ወደ 17 ነጥብ 2 ለማሳደግ ቢሆንም በእቅዱ ሶስት አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ 11 ነጥብ በታች ድርሻ ብቻ ላይ ነው መድረስ የተቻለው ።

በፓርላማው በአምስት አመት ይሰበሰባል ተብሎ የተቀመጠው የ599 ቢሊዮን ብር ከትራንስፎርሜሽን እቅዱ ጋር ሲነፃፀር ግማሽ ያህሉ ነው።

ሚኒስቴሩ ያሉ ክፍተቶችን በቀረው አንድ አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ለማካካስና የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልፀዋል።

ግብር እንዲከፈል በተሰሩ የንቅናቄ ስራዎችም ገቢ አሰባሰቡ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም