በሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ በ25 ሚሊዮን ብር በጀት የመስኖ ፕሮጀክት ተጀመረ

64

ጅማ  መጋቢት 7/2011 በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ በ25 ሚሊዮን ብር በጀት የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክት ተጀመረ፡፡

ፕሮጀክቱ የሚካሄደው ሰፖርት ፎር ሰስተኔብል ዴቬሎፕመንት(SSD) በተባለ አገር በቀል ድርጅት አማካኝነት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡

የድርጅት ተጠባበቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተረፈ ሰይፈ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የሚገነባው ከሰዎች ለሰዎች ከተባለው ድርጅት በተገኘ 20 ሚሊዮን ብርና ቀሪው ከኦሮሚያ ክልል ግብርናና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ በተመደበ በጀት ድጋፍ ነው።

በያዝነው ሣምንት የተጀመረው ፕሮጀክት በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚህም 200 ሄክታር መሬት በማልማት 600 አባወራዎችን ተጠቃሚ እንደሚሆኑበት አቶ ተረፈ አስረድተዋል፡፡

የሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጠሃ ቀመር የመስኖ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ፣ጥራትና በጀት እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ  አረጋግጠዋል፡፡

ፕሮጀክቱ አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ፣ በአዝመራቸውና በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ያስችለናል ብለዋል፡፡

አርሶ አደር አቶ ጁንዲ አባቢያ በሰጠት  አስተያየት ፕሮጀክቱ  የተፈጥሮ ሃብትን በተለይም ወንዞችን፣ለም መሬትንና የአየር ንብረቱን በአግባቡ ለመጠቀም እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በተያዘለት ጊዜም እንዲጠናቀቅ የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁነታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ሌላው አርሶአደር አቶ ከበደ ሲሳይ የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ አርሶአደሮች ከፍጆታ ምርት ይልቅ፤ ለገበያ የሚሆኑ ምርቶችን በማምረት ገቢያቸውን እንደሚያሳድግላቸው አስታውቀዋል፡፡

የአካባቢውም ኅብረተሰብም ዘላቂ ጥቅም በሚሰጥ የልማት ሥራ በመተባበር ግንባታው ለማጠናቀቅ ዝግጁ እንዲሆነም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም