በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት እያበበ መጥቷል-ዘ ኢኮኖሚስት

78

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2011 በኢትዮጵያ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ለፕሬስ ነጻነት ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል ሲል ዘ-ኢኮኖሚስትገለጸ።

ኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነትን በማክበር የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲያንጸባርቁ ምቹ መደላድል መፍጠሯን መጽሄቱ በዛሬ ዕትሙ አስነብቧል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1993 ኢትዮጵ የሚለውን ጋዜጣ በመክፈት ወደ ዘርፉ የተቀላቀለውን እስክነድር ነጋን ያስታወሰው መጽሄቱ ጋዜጣዋ ከሰባት ዕትም በኋላ ታግዳለች ብሏል።

እስክንድር እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2012 በሽብር ወንጀል ተከሶ 18 ዓመት ተፈርዶበት እስር ቤት መግባቱንና በቅርቡ ከእስር ተፈትቶ ወደ ሙያው መመለሱንም ጠቅሷል።

አገሪቱ ከመጋቢት 2010 ዓም አንስቶ የተለያየ አመለካከት ላላቸው በመቶዎች ለሚቆጠሩ ድረ-ገጾች፣ ብሎገሮች፣ ሳተላይት ቴሌቪዥኖች ፈቃድ በመስጠት በነፃነት እንዲሰሩ መፍቀዷንም ጠቅሷል።

በአገሪቱ ከ13 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ አለመኖሩንም አመላክቷል።

በተጨማሪ ከሐምሌ 2010 ዓም አንስቶ 23 የህትመት ውጤቶች ስድስት የግል የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በኩል ፈቃድ ተሰጥቷቸው ስራ ጀምረዋል።

በአገሪቱ የተፈጠረውን የለውጥ ንፋስ ተከትሎ በሶማሌ ክልል ለሚታተም የመጀመሪያው ነጻ ጋዜጣ ፈቃድ መሰጠቱም ተገልጿል።

ተፎካካሪ ፓለቲከኞችም በአገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሀሳባቸውን በነጻ እንዲያንጸባርቁ እድል አግኝተዋል።

በአገሪቱ በቅርቡ አዲስ የመገናኛ ብዙሃን መተዳደሪያ ደንብ ይወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅና ደንቡ የቅጣት ህጎቹን በማላላት፤ እንዲሁም የግሉ ኢንቨስትመንት በዘርፉ በስፋት እንዲሳተፍ ዕድል እንደሚከፍት ይጠበቃል።

ኢህአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት አንጻራዊ የፕሬስ ነጻነት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው በወቅቱ 200 ጋዜጦች፣ 87 መጽሄቶች ፈቃድ ተሰጥቷቸው ነበር ብሏል።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2010 እስከ 2015 ባለው ጊዜ 60 ጋዜጠኞች አገራቸውን ለቅቀው መውጣታቸውም ተጠቅሷል።

የህትመት ውጤቶች ዋጋ ካለፈው ታህሳስ ጀምሮ 50 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል።

መንግስት በወረቀት ላይ የጣለው ቀረጥ ከፍተኛ መሆንና የማስታወቂያ እጦት ለዘርፉ ተግዳሮት በመሆኑ መንግስት መልሶ ሊያጤነው እንደሚገባም በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል።

የመንግስት ሚዲያዎች በቀጣይ ለመንግስትና ለተፎካካሪ ፓርቲ ተጠሪዎች እኩል ጊዜ በመስጠት ሐሳባቸውን ማስተናገድ እንደሚጠበቅባቸው በዘገባው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም