ምክር ቤቱ በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ባለ የዋስትና መብት ረቂቅ አዋጅ ላይ ውሳኔ አሳለፈ

123

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2011 የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ባለ የዋስትና መብት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።

ረቂቅ አዋጁ ዋስትናው የተጠበቀ ዘመናዊ የብድር ሥርዓት ግለሰቦችና ተቋማት ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በማስያዝ ሥራ ላይ የሚውል አዲስ ካፒታል ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው።

የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግና ለማስፋፋት በዋስትና አስይዞ ብድር ማግኘት የሚቻልበትን ሥርዓት መዘርጋትና የማስፈፀሚያ መንገዱንም ቀልጣፋና ውጤታማ ማድረግ ተገቢ መሆኑን በረቂቅ አዋጁ ተመልክቷል።

በዚህም ለዋስትና በተያዘ ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ በተወዳዳሪ ባለመብቶች የሚነሳ የቀዳሚነት መብትን ለመወሰን የሚያስችል ወጥና ሁሉን አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ተወያይቶ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ይፀድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም