የጌዴኦ ተፈናቃዮች እርዳታ አላገኙም የተባለው መረጃ ሐሰት ነው – የሰላም ሚኒስቴር

1235

አዲስ አበባ መጋቢት 7/2011 የሰላም ሚኒስቴር የጌዴኦ ተፈናቃዮች ለስምንት ወራት እርዳታ አላገኙም በሚል በመገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው መረጃ ሐሰት ነው አለ።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ከመጋቢት 2010 ዓም ጀምሮ ከምዕራብና ምስራቅ ጉጂ እንዲሁም ከጌዶኦ ዞኖች 800 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ተፈናቅለዋል።


የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የጌዲኦ ተፈናቃዮችን አስመልክተው የሰጡት መግለጫ

ሚኒስቴሩ የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎችን በማስተባበርና ለጋሽ ድርጅቶችን ያካተተ ብሄራዊ ኮሚቴ በማቋቋም ተፈናቃዮቹ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙና ወደመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህም ከምስራቅ ጉጂ ከመጡ 13 ሺህ ተፈናቃዮች በስተቀር ከምዕራብ ጉጂ እና ከጌዴኦ ዞን ወደ ምዕራብ ጉጂ የተፈናቀሉ ዜጎችን በጊዜያዊነት ወደመጡባቸው አካባቢዎች ለመመለስ የሚያስችል ስራ መሰራቱን ነው የተናገሩት።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያዎች እንዲቆዩና ሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙም ተደርጓል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰየመ የፌዴራል ተቋማትን ያካተተ ግብረ-ሃይል ወደ ጌዴኦ ዞን በመሄድ ከተፈናቃዮች ተወካዮች ጋር በትናንትናው ዕለት ውይይት ማካሄዱን ገልጸዋል።

በውይይቱም ተፈናቃዮቹ ለስምንት ወራት እርዳታ አያገኙም ነበር የተባለው መረጃ ሐሰት ስለመሆኑ ከመግባባት ላይ መደረሱን ገልጸው

ይህንን አይነት ዘገባ ሲያቀርቡ የነበሩት መገናኛ ብዙሃንም ትክክለኛ መረጃ ይዘው አልነበረም ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

በአካባቢው የሚገኙት ተፈናቃዮች ቁጥራቸው ከ96 ሺህ እንደማይበልጥና መረጃዎችን የበለጠ የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአካባቢው ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በተለይም በጉጂ ወረዳዎች ለተፈናቃዮቹ የሚመጣውን እርዳታ በህገ-ወጥ መንገድ በመቀማት ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ የተደራጁ ቡድኖች እንደነበሩ በውይይቱ ላይ በተገኙ ተፈናቃዮች መገለጹንም ተናግረዋል።

ከተፈናቃዮቹ ጋር ተቀላቅለው በመጠለያዎች የሚኖሩና የሚመጣውን እርዳታ የሚጠቀሙ ሰዎች መኖራቸውንም በውይይቱ መነሳቱንም አክለዋል።

በዞኑ የታች መዋቅር የሚገኙ አንዳንድ አመራሮችም የእርዳታው አቅርቦት በአግባቡ እንዲዳረስ በማድረጉ በኩል አለመስራታቸውንም እንዲሁ።

በእነዚህ ችግሮች ሳቢያ አልፎ አልፎ ተፈናቃዮች ማግኘት የሚገባቸውን የምግብና ምግብ ነክ ድጋፍ ያለ ማግኘት ችግር ተፈጥሯል ነው ያሉት።

ሆኖም በጌዴኦ ዞን ወረዳዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች “የምግብና ምግብ ነክ እርዳታ መስተጓጎል ችግር አላጋጠማቸውም” ብለዋል። 

ወይዘሮ ሙፈሪያት እንደገለጹት በህገ-ወጥ አካላትና በእርዳታው ስርጭት በኩል እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ በሚኒስቴሩ በኩል ለአመራሮች አቅጣጫ ተሰጥቷል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጩ በረሃብ የተጎዱ የሴቶችና ህጻናትን የሚየሳዩ ፎቶዎችን በተመለከተ ትክክለኛውን መረጃ ለማጣራት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ በአካባቢው ከጤና እና ከውሃ ወለድ በሽታዎች ጋር ተያይዞ ችግሮች ያሉ ሲሆን በቀን እስከ አምስት ሰዎች በምግብ እጥረት ይሞታሉ የሚለው መረጃ ትክክል አይደለም።

ከውሃና ከጤና ጋር ተያይዞ ያሉት ችግሮች ለመፍታትም የጤና ሚኒስቴርና የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴሮች ቡድን አቋቁመው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው ላይ በቋሚነት ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ድጋፍ እያቀረበ ያለው ወርልድ ቪዥን መሆኑን ጠቅሰው ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች መልሶ ማቋቋም ላይ ያላቸው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአካባቢው የሚገኙ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የፌዴራል መንግስትና በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የህግ በላይነትን ለማረጋገጥና በህግ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ በሚሰሩ ስራዎችም በአካባቢው ነዋሪዎች በኩል ወንጀለኞችን የመደበቅ ችግር መኖሩንም አንስተዋል።