በሚዳ ወረሞ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ የተገኘ 516 ጀሪካን የምግብ ዘይት ተያዘ

230

ደብረብርሃን መጋቢት 7/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሚዳ ወረሞ ወረዳ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 516 ጀሪካን መያዙን ፖሊስ ገለጸ፡፡

የምግብ ዘይቱ የተያዘው መነሻውን አዲስ አበባ ያደረገው ታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3  – 58004  ኢ.ት ሲኖትራክ ተሽከርካሪ  በወረዳው ደጎሬ ቀበሌ እንደደረሰ መጋቢት 5/2011 ዓ.ም ምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ነው፡፡

በዞኑ ፖሊስ መምሪያ የቅድመ ወንጀል መረጃ ትንተና ኦፊሰር ዋና ሳጅን ሁሴን የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት የምግብ ዘይቱ የተገኘው ተሽከርካሪው 199 ቡልኬት እላዩ ላይ በመጫን ነው፡፡

በመንግስት ግዥ ገብቶ በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረብ የነበረበት ይሄው ባለ20 ሊትር 516 ጀሪካን የፓልም የምግብ ዘይት እንደጫነ የተያዘው ፈቃድም ሆነ ሌላ ህጋዊ ማስረጃ የለውም፡፡

ዘይቱ ሊያዝ የቻለውም  የአካባቢው ህዝብ እና ፖሊስ  በጋራ ባደረጉት ክትትል መሆኑን ዋና ሳጅን ሁሴን አመልክተው አሽከርካሪውም ተይዞ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡