ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ይሰጠን---ከምዕራብ ጉጂ የተፈናቀሉ የጌዲኦ ተወላጆች

135

ዲላ መጋቢት 6/2011 ከመኖሪያ ቦታቸው በመፈናቀላቸው ላጋጠማቸው ችግር በቂ ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑን በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ገደብ ወረዳ በመጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ገለጹ።


የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ዛሬ በስፍራው በመገኘት ከተፈናቃዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።


በውይይቱ ላይ ተፈናቃዮቹ እንደገለጹት ችግሩ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን ሳይፈታ በመቆየቱ ለብዙ ወራት በእንግልት ለመቆየት ተገደዋል።


መንግስት የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ቃል በመግባት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ቢያደርግም የፀጥታው ችግር ባለመፈታቱ ለአራተኛ ጊዜ መፈናቀላቸውን አስረድተዋል።


ከምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ የተፈናቀሉት አቶ ደመላሽ ግርማ እንደገለጹት ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ በተነገራቸው መሰረት ምንም አይነት የተመቻቸ ሁኔታ በሌለበት ተመልሰው የፕላስቲክ ሸራ በመወጠር መጠለያ ሰርተው መኖር ጀምረዋል።


ይሁን እንጂ በተለያየ አጋጣሚ የታጠቁ ኃይሎች ቤታቸውን በማፍረስና እንግልት በማድረስ ጫና ስለፈጠሩባቸው ዳግም ወደ ጌዴኦ ዞን ሊፈናቀሉ መቻላቸውንም ተናግረዋል።


ባለፈው አመት ችግሩ እንደተከሰተ መንግስት በዘላቂነት ለመፍታትና በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ቃል የገባ ቢሆንም እንግልቱ እስከ አሁን መቀጠሉን የተናገሩት አቶ ደመላሽ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሹም አስረድተዋል።


ሌላው ከቀርጫ ወረዳ የተፈናቀሉት አቶ ንጋቱ ጂግሶ "ወደ ቀያችን በምንመለስበት ወቅት የመንግስት ክትትልና የሕግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ በመሆኑ ዳግም ልንፈናቀል ችለናል" ብለዋል።


መንግስት በአፋጣኝ ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው በሰላም የሚኖሩበትን መንገድ ሊፈጥርላቸው እንደሚገባም አመልክተዋል ፡፡


የሠላም ሚኒስቴሯ በበኩላቸው ሁለቱ ክልሎችና የፌዴራል መንግስት ችግሩን ለመፍታት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀው "ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱም የተደረገው የፀጥታ ሁኔታውን ለማስተካከል ከነበረው ቁርጠኝነት የተነሳ ነው" ብለዋል ፡፡


መንግስት ጉዳዩን በዝምታ የሚያየው እንዳልሆነ የተናገሩት ወይዘሮ ሙፈሪሃት ችግሩ በታሰበው ልክ ፈጥኖ ሊፈታ አለመቻሉን  አስረድተዋል ፡፡


የሚሰራው ሥራ እንዳልቆመ የተናገሩት ሚኒስትሯ "የህዝቡን ሠላም እስከ መጨረሻው እስክናረጋግጥ ድረስ የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል ፡፡
ለተፈናቀሉ ዜጎች በቂ ሰብአዊ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነም ገልጸው የህክምናና የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦቱን የተሟላ ለማድረግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ክልሎች ቡድን በማዋቀር እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም