የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ምህንድስና ትምህርት ክፍል ሊከፍት ነው

86

መቀሌ መጋቢት 6/2011 የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምህንድስና ትምህርት ክፍል ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ።

በአድዋ ከተማ በ60 ሚሊዮን ብር እየተገነባ የሚገኘው የትምህርት ክፍሉ ህንጻ በመጪው ሰኔ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር  ጸሐዬ አስመላሽ ለኢዜአ እንደገለጹት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት  ምህንድስና ትምህርት ክፍል መክፈት ያስፈለገው የዘርፉ ኢንዱስትሪ   በምርምርና ጥናት እንዲታገዝ  ለማስቻል ነው።

"በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ፍላጎት እያደገ መጥቷል" ያሉት ዶክተር  ጸሐዬ የትምህርት ክፍሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ዘርፍ በእውቀትና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በአዲሱ የትምህርት ክፍል በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር  የሚያገለግሉ  ግብዓቶችን የሟሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑ አስረድተዋል፡፡

የትምህርት ክፍሉ በተያዘው የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራውን ለመጀመር በእቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በግንባታ መጓተት ምክንያት ስራ መጀመር አለመቻሉን አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ቴድሮስ ይትባረክ የስራ የተጓተተው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያጋጠመውን የግንባታ  እቃዎች ግብዓት እጥረት እና ፕሮጀክቱ ያረፈበት የቦታ ጥበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግሮቹ በመፈታታቸው  የትምህርት ክፍሉን  ግንባታዎች እስከመጪው ሰኔ ወር  ለማጠናቀት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ቴድሮስ  እንዳሉት የተማሪዎች መማሪያ ክፍሎች ፣ ቤተመጻህፍት፣ ቤተ ሙከራ እና ሁለት የተማሪዎች የመመገቢያ አደረሾች  ግንባታ ተጠናቋል፤ባለ አራት ወለል  የያዙ ሁለት የተማሪዎች መኝታ ክፍሎችና የተማሪዎች መማሪያ ህንጻዎች ግንባታ እየተገባደደ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ምህንድስና ትምህርት ክፍል ለመክፈት መዘጋጀቱ  ለዘርፉ ኢንዱስትሪው እድገት የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ በዓድዋ ከተማ የሚገኘው የአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ተክለማርያም ተስፉ ናቸው፡፡

"የምህንድስና ትምህርት ክፍሉ በአልመዳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አቅራቢያ መገንባቱ ተማሪዎች  በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል "ብለዋል፡፡

በፋብሪካው ያሉትን ማሽነሪዎች እና አሰራሮችን በማየትና ችግሮችን በመለየት የተሻለ ክህሎት እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ስራ አስክያጁ ተናግረዋል፡፡

በአደዋ ከተማ የአብነት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዘመም ፍስሃ  የዩኒቨርስቲው በዓድዋ ከተማ  የትምህርት ክፍል መክፈቱ ስራ እድል እንደሚፈጥር እና ለከተማዋ እድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖውም ገልጸዋል።

የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በትግራይ ክልል   ሃያ የሚሆኑ ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በዘርፉ ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም