ሙስናን ለመግታት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግንባር ቀደም ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

383

አምቦ መጋቢት 6/2011 ሙስናን ለመግታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያዘጋጀው ጉባኤ ትናንት በአምቦ ከተማ ተካሂዷል።

የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አየልኝ ሙሉዓለም በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት በሙስና እንዳይደናቀፍ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የትምህርት ተቋማቱ በሥነ ምግባር የታነጸና ሙስናን የሚጸየፍ ዜጋን በማፍራት በኩል ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

የዩኒቨርሲቲ አመራሮች በተቋማቸው የሚታዩ የአሰራር ብልሹነቶችን በቀዳሚነት ተከታትሎ ከማረም ባለፈ ለሙስና አጋላጭ ከሆኑ ድርጊቶች ራሳቸውን በመቆጠብ በአርአያነት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ተናግረዋል።

“ኮሚሽኑ የሥነ ምግባር ትምህርትን በመላ ሀገሪቱ ለማስፋፋት እየሰራ ነው” ያሉት ኮምሽነሩ የህጻናትና ወጣቶች ስነ-ምግባር ግንባታ ስትራቴጂ ተቀርጾ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱንም ጠቁመዋል።

ከማህበረሰብ አደረጃጀቶች፣ ከብዙሀን መገናኛና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ጥምረት በመፍጠር የስነ-ምግባር ግንባታና የፀረ ሙስና ትግሉን ለማቀጣጠል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ በበኩላቸው ሙስናና ብልሹ አሰራር በአንድ ተቋም ብቻ ሊገታ ስለማይችል ሁሉም አካላት ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

“በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመደበውን  ሀብት ለታለመለት ዓላማ በማዋል ለሀገሪቱ እድገት አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።

ሙስናን ማስቀረት ባይቻልም ለመቀነስ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ የተገነባው የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ተወካይ አቶ ሚሊኬሳ ቡልቶ ናቸው።

በጉባኤው ላይ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች፣ መምህራን፣ የተማሪ ተወካዮች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የሃገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የሙስና፣ የሥነ ምግባርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ።