ምክር ቤቱ ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተደረገውን የብድር ስምምነት አጸደቀ

48
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ እና ለከተሞች ተቋማዊና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር የተገኘውን ብድር ስምምነት አጽድቋል። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው የ3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 27ኛ መደበኛ ስብሰባ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም 1086/2010 በአንድ ድምጸ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ፤ ለከተሞች የተቋማዊና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም 1087/2010 ብድር ስምምነት በተመሳሳይ በአንድ ድምጸ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። ለኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በመደበኛ ብድር 250 ሚሊዮን ዶላር፣ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ብድር ደግሞ 125 ሚሊዮን ዶላር የሚሰጥ ስምምነት እንደሆነ የምክር ቤቱ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ ገልጸዋል። ለከተሞች የተቋማዊና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የሚውል የ127 ሚሊዮን ዶላር በመደበኛ ብድርና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ብድር እንዲሁ 200 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት እንደሆነም አክለዋል። የመሰረተ ልማት ብድሩ የሚውለው ለተመረጡ 117 ከተሞች የመሰረተ ልማት እድገትና አገልግሎት ማሻሻያና የተቋማትን አቅም በማሳደግ የከተሞችን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ለማጎልበት እንደሆነ ገልጸዋል። በተመሳሳይም ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ብድሩ በገጠር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አማራጭ የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግና ከግብርና በተጨማሪ የሙያ መስኮች እንዲሰማሩ እድል ለመፍጠር መሆኑን ምክትል ሰብሳቢው አስገንዝበዋል። የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግና የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በሚያስችል መልኩ ብድሩ አገልግሎት ላይ እንደሚውልም ጠቁመዋል። በመደበኛ የተገኘው ብድር ወለድ የማይከፈልበት እንደሆነና የስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ ነው ። የተገኘው ብድር  በገበያ ዋጋ ብድር የሚመሰረት ሆኖ የዘጠኝ ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ30 ዓመታት ተከፍሎ የሚያልቅ እንደሆነ ምክትል ሰብሳቢው አብራርተዋል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ቅርንጫፎችን ለመክፈት የተዘጋጀውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ 15/2010 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ቅርንጫፎቹ በሰመራ፣ አሶሳና ጋምቤላ የሚከፈቱ ናቸው ተብሏል። የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የሁለት ዳኞች የስራ ስንብት ውሳኔ እንዲጸድቅለት ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ምክር ቤቱ ለህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። የሳውዲ አረቢያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የቤት ሰራተኞች ቅጥር ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ አባላት ሰነዱ ባለመድረሱ ለሌላ ቀን እንዲዛወር ተደርጓል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም