ከምስራቅ ወለጋና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ እየተሰራ ነው

458

ነቀምቴ/ጎንደር መጋቢት  6/2011 በምስራቅ ወለጋ ዞን ተጠልለው የነበሩ 27ሺህ 314 ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

በተመሳሳይ በማዕከላዊ ጎንደር በጊዚያዊ መጠለያዎች የቆዩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ  እና ኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው ከነበሩ ወገኖች መካከል የተወሰኑት ሰሞኑን መመለሳቸው ተነግሯል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ እንዳስታወቁት ከአዋሳኝ ወረዳዎቹ ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች ከነበሩት መካከል 22ሺህ 164 ቤተሰብ ያላቸው 5ሺህ 150 አባ ወራዎች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል።

” የህዝብን ሰላም በማይፈልጉ ኃይሎች በአዋሳኝ አካባቢዎቹ ተከስቶ የነበረው አለመግባባት በአሁኑ ወቅት በመፈታቱ ተፈናቃዮች እንዲመለሱ ተደርጓል ” ብለዋል ።

በየጊዜው የተካሄዱ የሠላም፣ የልማትና የእርቅ ኮንፈራንሶች በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጾ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ ቀሪዎቹን በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን የማስመለስ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ወደ መኖሪያ ቄያቸው የተመለሱ ወገኖች በምግብ እህል ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ከመንግሥት የሚደረግላቸው ድጋፍ ይቀጥላል ” ያሉት ደግሞ የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳርጌ ጉደታ ናቸው ፡፡

በሳሲጋ ወረዳ ከአንዱራ በሎ ቀበሌ 1ኛ ካምፕ ተፈናቅለው በበሎ መጠለያ ጣቢያ ከነበሩት መካከል አቶ ገመዳ ፊጤ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት እርቀ ሰላም በመውረዱ መደ ቀያቸው ተመልሰዋል።

“ከሁለት መኖሪያ ቤቶች መካከል አንዱ ከነማድቤቱ ሳይቃጠል በመተረፉ ከሦስት ቤተሰቦቼ ጋር ወደ ቀድሞ ኑሮዬ ተመልሻለሁ” ብለዋል ።

ወይዘሮ ዜይኒ መሐመድ በበኩላቸው ከቆዩበት በሎ መጠለያ ጣቢያ አራት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው መንደር 10 ወደተባለ የቀድሞ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ዜና በማዕከላዊ ጎንደር በጊዚያዊ መጠለያዎች የቆዩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በአይምባ ጊዚያዊ መጠለያ የቆዩ ተፈናቃዮችም በአካባቢያቸው አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ በራሳቸው ፍላጎት ወደ ቀያቸው መመለስ እንደጀመሩ ገልጸዋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መንበሩ አውደው እንዳሉት ከተፈናቃዮች ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት ፈቃደኛ የሆኑ አባወራና ቤተሰቦቻቸውን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ ተጀምሯል፡፡

“ከትላንት ጀምሮ በአይምባ ጊዚያዊ መጠለያ የነበሩ 770 አባወራና ከ3ሺህ በላይ ቤተሰቦቻቸው በተዘጋጀላቸው ተሽከርካሪ አንከራና ላዛ ወደ ተባሉ ሁለት ቀበሌዎች እንዲጓጓዙ ተደርጓል” ብለዋል፡፡

ከምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ተፈናቅለው በአይምባ ጊዚያዊ መጠለያ የቆዩ አባውራና ቤተሰቦቻቸውን ላዛ ወደ ተባለው የመኖሪያ ቀያቸው ለማጓጓዝ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

“ለተፈናቃዮች የአንድ ወር ቀለብ የሚሆን 6ሺህ ኩንታል 837 ስንዴና ሩዝ፣ 1ሺህ 412 ኩንታል አልሚ ምግብና 200ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት  ተከፋፍሏል” ብለዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ተፈናቃዮች ፈጥነው ወደ እርሻ ስራ መግባት እንዲችሉ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ልዩ ልዩ የእርሻ መሳሪያዎችን በመኖሪያ ቀያቸው የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው።

አርሶ አደር አሰፋ ጸጋው ከጭልጋ አካባቢ ከነቤተሰባቸው ተፈናቅለው በአይምባ ጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሁለት ወር መቆየታቸውን ገልጸዋል።

አካባቢያቸው ሰላም በመሆኑ በፍቃዳቸው ወደ ቀያቸው ለመመለስ መወሰናቸውን የገለፁት አርሶ አደሩ “በግጭቱ ንብረቴን አጥቻለሁ፣ ፈጥኜ መቋቋም እፈልጋለሁ” ብለዋል ።

በጭልጋ ወረዳ የላዛ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አቡሃይ አለሙ በበኩላቸው ወደ ቀየቻው ተመልሰው መደበኛ ሕይወት ለመጀመር ከፍተኛ ጉጉት እንደደረባቸው ተናግረዋል፡፡

“ወደ መደበኛ የእርሻ ሥራ እንድንገባ መንግስት የቅርብ ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባል” ብለዋል፡፡

በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በተፈጠረው ግጭት 49ሺህ 500 ተፈናቃዮች በጊዚያዊ መጠለያና ከዘመድ ጋር ተጠግተው እንደሚገኙ ተገልጿል።

በዞኑ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ሥራ ከ30 እስከ 40 ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ የማስፈጸሚያ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ለማወቅ ተችሏል።