የህንድ መንግስት በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ለ3ሺህ500 ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል ይሰጣል

785

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 የህንድ መንግስት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2019 ብቻ ለ3ሺህ500 ያህል ኢትዮጵያውያን ነጻ የትምህርት እድል ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

‘ስተዲ ኢን ኢንዲያ’ በተሰኘው ተቋም አማካኝነት የሚሰጠው የትምህርት ዕድል የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠናን ያካተተ እንደሚሆን ታውቋል።

የህንድ መንግስት በሚሰጠው ነጻ የትምህርት ዕድል ከመላው አፍሪካ ተጠቃሚ የሚሆኑ ዜጎች ቁጥር ከ20 ሺህ የሚልቅ እንደሆነ ‘ስተዲ ኢን ኢንዲያ’ አስታውቋል።

ትምህርትና ስልጠና የሚሰጥባቸው መስኮች በርካታ ሲሆኑ የህክምና ዘርፍን የማያካትት መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኑራግ ስሪቫስታቫ እንደገለጹት፤ የህንድ መንግስት ለአፍሪካ አገሮች እየሰጠውን ያለው የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጠና አጠናክሮ የማስቀጠል ፍላጎት አለው።

አክለውም ተቋሙ አጫጭር ስልጠናዎችን በማዘጋጀትና ነጻ የትምህርት እድል ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ገልጸው አሁን ደግሞ በፊት ይሰጠው የነበረውን ቁጥር በማስፋትና ረጅም ስልጠናዎችንም ለመስጠት ማሰቡን ገልጸዋል።

38 ሺ ኮሌጆችና 800 ዩኒቨርሲቲዎች ያሏት ህንድ በትምህርት ተቋማት ብዛትና የትምህርት እድሎችንም በማመቻቸት ረገድ ትታወቃለች።