በኢሉአባቦር አዲስ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው

100
መቱ ግንቦት 23/2010 በኢሉአባቦር ዞን ብስባሽና የእንስሳት ፍግ በአጭር ጊዜ የሚያብላላ አዲስ  የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጃጀት ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ ተገለጸ፡፡ እስካሁንም  በአርሶ አደሩ የተዘጋጀ  900 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ ጽህፈት ቤቱ እንዳለው አዲሱ አዘገጃጀት  ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኘ  የትል ዝርያ ሰዎችን በመተካት  ማንኛውንም ብስባሽና የእንስሳት ፍግ በአጭር ጊዜ በማብላላት ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያነት የሚለውጥ ነው፡፡ ትሉን  በመጠቀም የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበርያ የአፈር ለምነትን በተሻለ ደረጃ የሚጨምር ከመሆኑም በተጨማሪ  የአርሶአደሩን ጊዜና ጉልበት እንደሚቆጥብ ተመለክቷል፡፡ ትሉን  በማራባት ማዳበሪያውን ማዘጋጀት በሚቻልበት ላይ በዞኑ  31 የገጠር ቀበሌዎች በ41 አርሶአደሮች ማሳ እና በአንድ   ማሰልጠኛ ጣቢያ በተግባር የተደገፈ ስልጠናና የማስተዋወቅ ስራ እየተካሄደ መሆኑን  በጽህፈት ቤቱ የአፈር ለምነትና ስርጸት ቡድን መሪ አቶ ሂርጶ ሞርካ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓይነት ዘዴ እስካሁን 900 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ መዋሉን ያመለከቱት አቶ ሂርጶ በዚህ ስራም በዞኑ 13 ወረዳዎች የሚገኙ ከ100 ሺህ በላይ አርሶአደሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ጥቅም ላይ የዋለው በቡና ልማት እና በመኸር  ወቅት በሚለማ  90 ሺህ ሄክታር  መሬት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ " የተፈጥሮ ማዳበርያ ለአፈር ለምነት ካለው ጠቀሜታ አንጸር አርሶአደሩ በስፋት በማዘጋጀት ጥቅም ላይ እንዲያውል ተከታታይ ትምህርት ከመስጠቱ በተጓኝ የማዘጋጀቱም ስራ ቀጥሏል" ብለዋል፡፡ አርሶ አደር ጥላሁን ጆቴ በዞኑ አሌ ወረዳ የኦንጋ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ዘንድሮ ከመስከረም እስከ ህዳር ባሉት ወራት 50 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ለቡና እና መስኖ ልማት መጠቀማቸውን  በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በብዛት ያለማዘጋጀታቸው የፋብሪካ ማዳበሪያ ብቻ ገዝተው ለመጠቀም  ይገደዱ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደሩ" ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ይጠቅማሉ የተባሉት የትል ዝርያዎች ቢቀርቡልኝ አባዝቼ ለመጠቀም ዝግጁ ነኝ "ብለዋል፡፡ በኢሉአባቦር በ2010/2011 የምርት ዘመን  ከ132 ሺህ  አርሶአደሮችን   በማሳተፍ ከ145 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ  መሬት በተለያዩ ሰብል ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን  የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም