ከከፍተኛ የውሃ ተጠቃሚ ድርጅቶች የውሃ ፍጆታ በመቀነስ የማመጣጠን ስራ ተጀመረ

366

አዲስ አበባ መጋቢት 6/2011 የከተማዋን የመጠጥ ውሃ እጥረት ለማቃለል ከከፍተኛ ውሃ ተጠቃሚ ድርጅቶችና የልማት ፕሮጀክቶች የውሃ ፍጆታ ቀንሶ ለከተማዋ ነዋሪ በማዳረስ የማመጣጠን ስራ መጀመሩን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።

የከተማዋ የውሃ ፍላጎት 930 ቢሆንም የባለስልጣኑ የማምረት ዓቅም 574 ሺህ ሜትር ኩብ የመጠጥ ውሃ ነው።

ከሚያመርተው ውስጥ ተጣርቶ ወደ ተጠቃሚው የሚደርሰው 525 ሺህ ሜትር ኩብ ብቻ እንደሆነ ባለስልጣኑ ይገልጻል።

ለተጠቃሚ ከሚደርሰው ውሃ ውስጥ አብዛኛውን የሚጠቀሙት የባለስልጣኑ አንድ በመቶ ደንበኞች የሆኑት የመንግስትና የግል ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች መሆናቸውን የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል።

99 በመቶ የሚሆነውን የባለስልጣኑ ደንበኞች ፍጆታ እንዲጨምር እነዚህ ድርጅቶች የራሳቸው የውሃ ጉድጓድ እንዲኖራቸው ከባለስልጣኑ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

የባለስልጣኑ የከፍተኛ መስመርና የውሃ ስርጭት ሲስተምና ብክነት ቁጥጥር የስራ ሂደት አቶ ዘላለም ፀጋዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ የከተማዋን የውሃ ችግር አጥንቶ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ ችግሩ ለመፍታት እየሰራ ይገኛል።

በመፍትሄነት የተለዩት ከፍተኛ የውሃ ፍጆታ ያላቸው ድርጅቶች የራሳቸውን የውሃ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ ድጋፍ ማድረግ፣ የመጠጥ ውሃንና የልማት ስራ ውሃን መለየትና ተጨማሪ ጉድጓዶችን መቆፈር በረዥም ጊዜ እቅድ ተይዘው እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

ቡድን ተዋቅሮ የድርጅቶቹ የውሃ አጠቃቀምና ፍላጎት ክትትል እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዘላለም በአንዳንድ ድርጅቶች ከውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም እንደ ሆስፒታልና ሌሎች ከህዝብ አገልግሎት ጋር የተያያዙና ስራቸው ከውሃ ጋር እጅጉን የተቆራኘ ድርጅቶችን በማይጎዳ ሁኔታ በጥናት ላይ  የተመሰረተ የማመጣጠን ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ማስተካከያው በተለይ ውሃ ያለ አግባብ የሚያባክኑትን፣ ከሚገባቸው በላይ የወሰዱትን የሚመለከት ሲሆን ተቀናሽ የሚሆነው ውሃ ለከተማዋ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ መሟያ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የውሃ እጥረቱን በዘላቂነት ለመቀነስ ለኮንስትራክሽንና ለሌሎች የልማት አገልግሎት የሚውል ሌላ የውሃ አማራጭ ለመዘርጋት ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝም አቶ ዘላለም ገልጸዋል።

ከፍተኛ የውሃ ተጠቃሚ ድርጅቶች የራሳቸውን የውሃ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ በተደረገው ጥረት ባለፈው አንድ አመት 31 የሚደርሱ ድርጅቶች ወደ ተግባር መግባታቸውንም አቶ ዘላለም ተናግረዋል።